ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ውልደት እና እድገቴ ጎጃም ነው። ከልጅነት እስካኹን ድረስ በብዙ ድግስ ቤቶች ተገኝቼ ቃርሜአለሁ። ከውልደት እስከ ዕድገት በተገኘሁባቸው ድግሶች አንድ የታዘብሁት ትልቅ ጉዳይ አለ፤ እሱም አቆልቋይ ወይም ሌማት ተብሎ ይጠራል። በጎጃም ሕዝብ በተለይም በገጠሩ ማኅበረሰብ አቆልቋይ ወይም ሌማት እስካኹንም ድረስ የተለመደ ነው።
በጎጃም እና አካባቢው ባሕል መሠረት ሰርግ እና ተዝካር ብዙ የድግስ ወጭ ይጠይቃል። ለዚህም ማሳያ የሚኾን ተዝካርን ልጥቀስ። በጎጃም በተለይም አንድ ሰው ሀዘን ወደ ቤቱ ሲገባ የአካባቢው ማኅበረሰብ ሀዘኑን ከመጋራት አልፎ በመረዳዳትም ያምናል። አብሮ እንደ ቤተሰብ ደረቱን ደቅቶ፣ ወዬ ብሎ አልቅሶ ይቀብራል። እዝኑን በየቀኑ ይዞ እየቀረበ ሀዘንተኞችን ያጽናናል። በተለይም ደግሞ የሟች ተዝካር (የአርባ ቀን መታሰቢያ) የሀዘንተኛው የቅርብ ዘመዶች፣ ጎረቤቶች እና ባልንጀሮች የድግሱን ሸክም አብረው ይጋራሉ።
የቅርብ ዘመዱ እና ወዳጁ እንደየአቅሙ አንድ እንስራ ጠላ ወይም ሁለት እንስራ ጠላ (ግማሽ አቆልቋይ) አልያም አንድ አቆልቋይ (ሙሉ ሌማት) ወይም ሁለት አቆልቋይ ልያዝ ወይም ልስጥ ብሎ ይጠይቃል፡፡ ጠያቂው ከዚህ በፊት ደጋሹ አቆልቋይ የያዘለት በመኾኑ እሱም የድርሻውን የሚጠበቅበትን ለመመለስ በማሰብ ወይም ደግሞ እንደ አዲስ ለመጀመር የፈለገ ሊኾን ይችላል፡፡
አንድ አቆልቋይ ወይም ሙሉ ሌማት ማለት 100 እንጀራ፣ 100 ሊትር ጠላ ወይም በግምት 25 ሊትር የሚይዝ አራት እንስራ ጠላ እና አንድ በገፈጅ ወጥ ሲኾን ይህም በትንሹ መቶ እንግዶችን ያስተናግዳል ተብሎ ይታሰባል፡፡ አቆልቋይ ወይም ሌማት የሚይዝ ሰው የቅርብ ነዋሪ ብቻ አይደለም። ከቆላ እስከ ደጋ አልያም ከደጋ እስከ ቆላ ጠላ (ድፍድፍ) እና እንጀራውን በበቅሎ፣ በፈረስ፣ በአህያ ጭነው ወይም ራሳቸው ተሸክመው ብዙ ርቀት ይጓዛሉ። እነዚህ ሰዎች ያዘጋጁትን ድፍድፍ እና እንጀራ ጭነው ይመጡና ከድግሱ ቤት ቀሪውን ሥራ የሚያጠናቅቁበት ልዩ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡
ወጥ የሚሠሩትም እዚያው ድግስ ቤት ከተሰጣቸው ቦታ ላይ ይኾናል፡፡ በዚህ ድግስ ላይ ደጋሾች ፍሪዳ ጥለው አቆልቋይ ወይም ሌማት ለያዙት ሰዎች ለወጥ የሚኾን ሥጋ ያከፋፍላሉ፡፡ ተዝካሩ በፆም ወቅት ከኾነ ግን የፆም ወጥ (የተለመደው ክክ ወጥ ነው፣ በጎጃም አጠራር ማርሳ ወጥ) አቆልቋዩን በያዙት ሰዎች ይሸፈናል።
አቆልቋይ ወይም ሌማት የያዙ ሰዎች ምግብ እና መጠጥ ሠርተው ብቻ ለባለጉዳዩ አይሰጡም፡፡ ይልቁንም በወሳኙ ሰዓት ላይ ተገኝተው ራሳቸው አስተናግዱልኝ (በጎጃም አገላለጽ አብላልኝ) ብሎ የመደበላቸውን ሰው የማስተናገድ ኀላፊነትም ጭምር አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ባለጉዳዩ አቆልቋይ ወይም ሌማት የያዘለትን ሰው ዕድርተኛዬን፣ ማኅበርተኛዬን ወይም ሰፈሬን አብላልኝ ሊለው ይችላል፡፡
የአቆልቋይ ወይም የሌማትን ባሕላዊ ሥርዓት በጥሩ ኹኔታ እንዲተገበር እንግዶች በታሰበው መልኩ ቦታ ቦታቸውን ይዘው እንዲቀመጡ ማድረግ ወሳኝነት አለው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አስተናጋጆች የተሰጣቸውን ኀላፊነት ለመወጣት ወዲያ ወዲህ ማለት የተለመደ ነው፡፡ እንግዶች በየማዕረግ እና በየዕድሜያቸው ነው የሚቀመጡት።
ሽማግሌዎች ከላይ ይቀመጣሉ፤ ሌሎችም በየማዕረጋቸው ቦታ ቦታቸውን ይይዙና መስተንግዶው ይጀመራል። ይበላል፤ ይጠጣል። ከመስተንግዶው በኋላ ሽማግሌዎቹ ነፍስ ይማር ብለው ይመርቃሉ። በጥቅሉ መስተንግዶው ጥሩ ባይኾንም ወይም ጠላው ቢበላሽ የሚወቀሰው ያበላው ባለ አቆልቋይ ወይም ባለ ሌማቱ እንጂ ባለጉዳዩ አይደለም፡፡
ተጋባዦችም እኛ እገሌ ጋር ነበር የተስተናገድነው ከሱ ዘንድ ነበር ነው የሚሉት፡፡ ይህ የአቆልቋይ ወይም የሌማት ባሕል በተለይም ድግስ በሰፊው ይደገስ በነበረበት ቀደም ባለው ጊዜ በባለጉዳዩ የሚያሳድረውን የጉልበት እና የወጭ ጫና በከፍተኛ ኹኔታ ያቃልላል፤ መተሳሰብን እና መተባበርንም አጎልብቶ ኖሯል።
በደመወዝ የቆዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን