“እርቁን የሚያፈርስ ጥቁር ውሻ ይውለድ”

0
66

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰዎች በሚያደርጓቸው ማኅበራዊ መስተጋብሮች ውስጥ ግጭት የማይቀር አንድ ክስተት ነው፡፡ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ታዲያ ሰዎች ራሳቸው ለእነዚህ ማኅበራዊ ክስተቶች መፍትሔ ሲዘይዱላቸው ይስተዋላል። በሀገሪቱ ግጭቶችን የሚፈቱ የተለያዩ የሽምግልና ሥርዓቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ለዛሬ ልናስቃኛቹህ የወደድነው ሰባቱ ከዘራን ነው።

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ እና አካባቢው ማኅበረሰቡ ለረጅም ጊዜ ሲጠቀምበት የቆየ ባሕላዊ የሽምግልና ወይም የግጭት አፈታት ሥርዓት ነው ሰባቱ ከዘራ። በልማት እና በጸጥታ ዙሪያ ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ የሚኾን ነገር ለመሥራት የሚንቀሳቀሱ አባቶች ነበሩ ይሉናል በሰባቱ ከዘራ የዞኑ የሽምግልና ሥርዓት ሠብሣቢ አየልኝ ክብረት። ሠብሣቢው እንደገለጹልን የሽምግልና ሥርዓቱ የቆየ እና ከ100 ዓመት በላይ ዕድሜ እንዳለው ይነገራል ብለዋል፡፡

የስያሜው አመጣጥ አንድ ሰው በመሃንዲስ የተሰጠው ቦታ ላይ ቤት ሢሠራ ከተፈቀደለት ፕላን ውጭ ለመሥራት ይነሳል፡፡ ለግለሰቡ ግንባታው ትክክል አለመኾኑን በማስረዳት እነዚህ ሽማግሌዎች ግንባታውን ያስቆሙታል፡፡ አጋጣሚ ኾኖ ሽማግሌዎቹ ሰባት ነበሩና ሁሉም ከዘራ ይዘው ነበር ይላሉ አቶ አየልኝ፡፡ በዚህ ጊዜም ግለሰቡ ሰባት ኾናችሁ፤ በሰባት ከዘራ አስቆማችሁኝ ብሎ ሲናገር ይህንን በመውሰድ ‘’ሰባት ከዘራ’’ የሚለው ስያሜ ተሰጥቶታል ነው ያሉን፡፡

ሰባቱ ከዘራ በባሕል እና በእምነት መሠረት የቆየ በሕዝቡ ዘንድ ግጭት ሲፈጠር፣ ወንጀል ሲፈጸም እና ሀገራዊ ችግሮች ሲኖሩ ሕዝቡ ውስጥ ሰላምን ለመፍጠር ሲከወን የኖረ እና አኹንም እየሠራ ያለ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡ እስካኹን ባለው ኹኔታ ሰባቱ ከዘራን ሕዝብ እና መንግሥት እንደ ትልቅ ማኅበራዊ እሴት ወስዶ ፍትሕን በማስፈኑ በኩል እየተሠራበት ያለ እና ማኅበረሰቡም ከመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ባልተናነሰ ሲዳኝበት ቆይቷል።

አንዳንድ ሀገራዊ ችግሮች ሲፈጠሩ ማኅበረሰቡን በማሥተባበር እና ችግሮችን ለመቅረፍ ማኅበረሰቡን በማንቃት፤ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዳይስተጓጎሉ በማድረግም መፍትሔ ሲኾን የቆየ ባሕላዊ እሴት እንደኾነ ሠብሣቢው ተናግረዋል፡፡ የመንግሥት ሥርዓት ሲላላ መደበኛ አገልግሎቱን እሰኪጀምር ድረስ የኅብረተሰቡ ሰላም ተጠብቆ እንዲቆይ የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ የቆየ ነውም ብለዋል፡፡

የሰባቱ ከዘራ ብዙ አባላት ያሉት ሲኾን ዞኑን ጨምሮ በሁሉም ወረዳዎች ይሠራበታል ነው ያሉት፡፡ ክዋኔውም ወጥነት እንዲኖረው የሁሉም ወረዳዎች የሰባቱ ከዘራ አባላት ተሠብሥበው ባጸደቁት አንድ አይነት ሕግ ወጥቶ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዚህ የሽምግልና ሥርዓት የሚስተናገዱ መሠረታዊ ጉዳዮች የግድያ ወንጀል፣ የትራፊክ አደጋ፣ የባል እና የሚስት ግጭት፣ የገንዘብ መካካድ እና የመሳሰሉት ናቸው ነው ያሉት፡፡

ለአብነት የግድያ ወንጀል በሚፈጸምበት ጊዜ ገዳዩ ቢሸፍት እና ቢጠፋ ዘመድ የኾነ ወንድም፣ የአክስት ልጅ፣ የአጎት ልጅ፣ ምንም በማያውቀው ደም ይመለስበት ነበር። በዚህ ጉዳይ ወንጀለኛው ተይዞ ለፍርድ ከቀረበ መልካም ይኾናል፤ ካልኾነ ግን ያልመከረ እና ያልዘከረ ዘመድ ቤተሰብ ይበተናል፤ ለተለያዩ ማኅበራዊ ቀውሶችም ይዳረጋል፡፡

ይህ እንዳይኾን ወንጀለኛውን በባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓቱ በማቅረብ ፍርድ ይሰጣል፡፡ በዚህም ሥርዓት የተቀመጡ ቅጣቶች አሉ፡፡ ለአብነትም ሳያስበው የግድያ ወንጀል ለፈጸመ 100 ሺህ ብር፣ አስቦ አልሞ ወንጀሉን ለፈጸመ 200 ሺህ ብር ካሳ ከፍሎ ታርቀው በሰላም እንዲኖሩ ይደረጋል፡፡ ይህንን ውል አፍርሶ የተገኘ ሰው ገንዘቡን እጥፍ አድርጎ ይመልሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከማንኛውም ማኅበራዊ ኑሮ ማለትም ከዕድር፣ ከማኅበር እና ከሌሎችም እንዲገለል ይደረጋል አሉን።

ከግድያ በተጨማሪ በስርቆት ወንጀል አንድ ሰው ሊሰርቅ ከሰው ቤት ሄዶ ያ ሰው ራሱን ለመከላከል በሌባው ላይ እርምጃ ቢወስድ የሟች ቤተሰብ ደም እመልሳለሁ እንዳይል የሚያደርግ ሥርዓት አጽድቀናል ብለዋል የእርቅ ሥነ ሥርዓቱ ሠብሣቢ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሌባ እና ነፍሰ ገዳይ የሚደብቅ ሰው ከተገኘ ልክ እንደወንጀለኛው ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ ይህም ወንጀልን መደበቅ እና ወንጀለኛን መደበቅ ልክ አለመኾኑን እና ሌላው ሰው እንዲማርበት በማሰብ ነው፡፡

የሰባቱ ከዘራ ሽማግሌዎች በሕዝብ የተመረጡ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ናቸው፡፡ ይህ የሽምግልና ሥርዓት ከዘመናዊ ጋር ሲነጻጸር ፍትሐዊነቱ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከፍተኛ እንደኾነ ነው አቶ አየልኝ የገለጹልን፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በፍርድ ቤት የሚወሰኑ ውሳኔዎች ማስረጃን መሠረት አድርጎ በመኾኑ በዚህም ብዙ ጊዜ በሐሰት ምስክር ፍርድ ተጓደለብን ብለው ስለሚያስቡ ነው ይላሉ። ከፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላም እርቅ አይመጣም፤ ደም የመመለስ ሃሳብ አለ ብለዋል፡፡

በሽማግሌ የሚሰጠው ፍትሕ ግን እውነቱ ወጥቶ እውነተኛ ፍርድ እና የተበደለን የሚክስ በመኾኑ ተመራጭ አድርጎታል ብለዋል፡፡ መጀመሪያ ለመታረቅ ያስቸግራሉ፤ ጊዜ ይፈጃል እንጅ ከታረቁ በኋላ ግን አያፈርሱም ነው ያሉት። በባሕላችን ይህንን ባሕላዊ እርቅ የሚያፈርስ ጥቁር ውሻ ይውለድ የሚል መሐላ ይዘን ስለምንሠራ ማኅበረሰቡ የሽማግሌዎችን ቃል አክብረው ይታረቃሉ፤ በሰላምም ይኖራሉ ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አየልኝ ገለጻ ይህንን ባሕላዊ እሴት ለመጠበቅ እና ለትውልድ እንዲተላለፍ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ባሕላዊ ፍርድ ቤት ለማቋቋም በጋራ ለመሥራት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ተብሏል፡፡ የባሕል እና ቱሪዝም እንዲኹም የሃይማኖት አባቶች ኅብረተሰቡ ከወንጀል እንዲርቅ የወንጀልን አስከፊነት ለማኅበረሰቡ የማስገንዘብ ሥራ እያከናወንን በጋራ እየሠራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

በሰባቱ ከዘራ በሚሰጠው የፍትሕ አገልግሎት ማኅበረሰቡ በመደበኛ የፍትሕ ሥርዓት ለማግኘት ከአላስፈላጊ ወጭ እና እንግልት እንዲኹም ከቂም በቀል እንዲርቅ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ነው ያሉት፡፡ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ እና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጋርም ሰላምን ለማስፈን በጋራ በመሥራታቸው ከማኅበረሰቡ እና ከመንግሥት ከፍተኛ ምሥጋናና ተቀባይነት ማግኘት ችለዋል፡፡

በሰሜን ጎንደር ዞን የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር የባሕል እሴት እና ኢንዱስትሪ ልማት ባለሙያ የሻረግ ዘነበ የሰባቱ ከዘራ የሽምግልና ሥርዓት የተለያዩ ግጭቶችን በመፍታት ደም እስከማድረቅ ድረስ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡ አስፈላጊነቱን እና ጠቀሜታውን አውቆ እንዲጠቀምበት እና እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ የባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም ነው የገለጹት፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሽምግልና ሥርዓቱ በተሻለ ኹኔታ እንዲሠራ የራሳቸው የኾነ ቢሮ እንዲኖራቸው ለማድረግ ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጋር በመነጋገር በጋራ እየሠራን እንገኛለን ነው ያሉት፡፡ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓቱን በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ ተሰንዷል፤ ምርጥ ተሞክሮ ተቀምሮ ለሚመለከታቸው አካላት ሰነዱ እንዲደርስ ተደርጓል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ይህንን ባሕላዊ እሴት ለማስተዋወቅ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ መኾኑን ገልጸውልናል፡፡

ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ እና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጋርም ሰላምን ለማስፈን በጋራ በመሥራታቸው ከማኅበረሰቡ እና ከመንግሥት ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት ችለዋል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ: ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here