የዘጌ ቀሚስ እና ጌጣጌጥ!

0
123

ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጣና ሐይቅ ላይ ክንፉን ዘርግቶ እንደተቀመጠ አሞራ የሚታየው ዘጌ፣ በጥንታዊ እና በሚያምሩ ባሕላዊ አልባሳቱ እና ጌጣጌጦቹ ይታወቃል። ከባሕር ዳር በጀልባ የአንድ ሰዓት ተኩል፣ በየብስ ደግሞ የሁለት ሰዓት ጉዞ ርቀት ላይ የምትገኘው ዘጌ፣ እናቶች እና ወጣት ልጃገረዶች እስካሁን ድረስ ውበታቸውን የሚገልጹባቸው እና መገለጫቸው የኾኑ ልዩ የአልባሳት እና ጌጣጌጥ አሏቸው።

ከዘጌ እናቶች የባሕላዊ አለባበሶች እና ጌጣጌጦች መካከል አንዱ ባለ ቁልፍ ቀሚስ ይሰኛል። ይህ ቀሚስ የዘጌ መለያ ተደርጎ ይወሰዳል። በአብዛኛው ለሙሽሮች በቤተሰቦቻቸው የሚዘጋጅ ሲኾን ከተጠለፈ በኋላ በብር የተሠሩ ቁልፎች በየጥልፉ እና ጠርዙ ላይ ተሰክተው ያጌጣሉ። ቀሚሱ በሀብት መገለጫነትም የሚታይ ሲኾን የብር ቁልፎቹ አኹን ላይ ከሌሎች ብር መሰል ቁሶችም ይሠራሉ።

ሌላው ልብ አልባ የሚባለው ቀሚስ ነው። ልብ አልባ ሴቶች ከቀሚስ ጋር የሚለብሱት ሱሪ ሲኾን ከሽመና የተሰራ ነው። ልክ እንደ ቀሚሱ፣ ከሱሪው ጫፍ ላይ በተለያዩ የክር አይነቶች ተጠልፎ ይለበሳል። ሳንቃ ድሪ የዘጌ ሴቶች የውበታቸው ማድመቂያ ጌጣጌጥ ነው። ሳንቃ ድሪ እጅግ ረዥም እና ሙሉ በሙሉ ከብር የሚሰራ የአንገት ጌጥ ነው።

ከፊትና ከኋላ እንዲወርድ ተደርጎ የሚሠራ ሲኾን ጠፍጣፋ ቅርጽ ያለው እና ዳር ዳሩን በትንንሽ ድብልቅ ጌጦች ያጌጠ ነው። እንደ የክት ጌጥ የሚታወቅ ሲኾን፣ የድሪው ጠፍጣፋ ክፍል ላይ ለኩል ማስቀመጫነትም ያገለግላል። የዘጌ ሴቶች ከሚያጌጡበት ሌላው ጌጥ የዘወትር ድሪ ይሰኛል። ይህ ድሪ በማንኛውም ቀን ከማንኛውም የዘወትር ልብስ ጋር የሚለበስ ነው።

እርባን ሌላው የጌጥ ዓይነት ነው። እርባን የአንገት ጌጥ ሲኾን ሴት ልጅ ስትዳር ከቤተሰቦቿ እና ከባሏ በጥሎሽ መልክ የምታገኘው ነው። ከብር የተሰራ እና በክር ተሰካክቶ ለማጌጫነት ይውላል።

✍ብር ቅጥል ነጭ ሽልንግ ይህ የጌጥ አይነት ከጠገራ ብር ሙሉ በሙሉ የተሠራ ነው። ይህንን ጌጥ የምታደርግ ሴት በትዳር የኖረች መሆኗን ያመለክታል።

✍አምባር አምባር ከብር የተሠራ የእጅ ጌጥ ሲኾን በሁለት እጅ የሚታሰር ነው። ለሙሽሮች የሚዘጋጅ እና በሰርጋቸው ቀን የሚያጌጡበት ባሕላዊ ጌጥም ነው።

✍ክት አልቦ አልቦ ከብር በክብ በክብ የሚሠራ ሲኾን በነጭ በተገመደ ማግ ተሰክቶ ለእግር ማጌጫነት ይውላል። በተለያዩ ባሕላዊ ቀናት፣ የሰርግ ቀን እና የገበያ ቀን የሚደረግ ባሕላዊ ማጌጫ ነው።

✍የዘወትር አልቦ ይህ የአልቦ አይነት ከብር የተሠራ እና በማንኛውም ቀን የሚደረግ የእግር ጌጥ ነው።

✍ስንድድ ስንድድ በክር ተሰክቶ በማንኛውም አዘቦት ቀን የሚደረግ የጌጥ አይነት ነው።

ዘጌ በባሕላዊ አለባበሶቿ እና ጌጣጌጦቿ ለትውልድ የሚተላለፍ ሲኾን እነዚህም ውበቶቿ ለሀገር ውስጥም ኾነ ለውጭ ጎብኝዎች ማራኪ እንደኾኑ ይታመናል።

ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here