ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ ወርቅ ማርያም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከሚገኙ ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ ናት፡፡ ደብረ ወርቅ ማርያም ከዞኑ ዋና ከተማ ደብረ ማርቆስ 114 ኪሎሜትር፣ ከክልሉ ዋና ከተማ ከባሕር ዳር 196 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በደብረ ወርቅ ከተማ የምትገኝ ታሪካዊ ገዳም ናት፡፡ ገዳሟ ከከተማዋ ዳርቻ ምሥራቃዊ አቅጣጫ ክብ ቅርጽ ባለው ኮረብታማ ቦታ ላይ ትገኛለች።
የእናርጅ እናውጋ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አሥኪያጅ እና የደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም አፈ መምህር ዓለምነው አዘነ ቤተ ክርስቲያኗ በ351 ዓ.ም መመስረቷን ይናገራሉ፡፡ እንደ አፈ መምህሩ ገለጻ ቤተ ክርስቲያኗ ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ ለክርስትና ሃይማኖት እና አስተምህሮ መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክታለች ነው ያሉት፡፡
ከዚያ በኋላ በ1372 ዓ.ም በአጼ ዳዊት አማካኝነት ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ ገዳም ኾኖ ሰፊ አሥተዳደር መዋቅር እንደተሠራለት ነው የገለጹት፡፡ በዘመናት ለውጥም የተለያዩ ነገሥታት አጼ ገላውዲዎስ እና በአጼ ተክለ ጊዮርጊስ እድሳት እንደተደረገላት ገልጸዋል፡፡ አሁን ያለው ቤተ ክርስቲያን በ1963 ዓ.ም በአጼ ኀይለ ሥላሴ እና በአካባቢው ማኅበረሰብ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኑ የሕንጻ ላይ ቅርጻ ቅርጾች፣ የግድግዳ ሥዕሎች እና የነገሥታት ገፀ በረከቶች የደብረ ወርቅ ማርያምን ጥንታዊነት የሚመሰክሩ ቅርሶች ናቸው፡፡
እንደ አፈ መምህሩ ገለጻ በወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የተሳሉት እና ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት የድንግል ማርያም ሥዕሎች “ወይኒት” በመባል የምትጠራው ስዕል በገዳሙ ውስጥ ትገኛለች፡፡
በገዳሙ ውስጥ በርካታ ሊጎበኙ የሚችሉ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች አሉ፡፡ እነዚህ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የደብር ሙዚየም ተገንብቶ ተደራጅተው ለጉብኝት ክፍት ኾነው ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
ከቅርሶች መካከል ከ300 በላይ የብራና መጻሕፍት፣ ከተለያዩ ነገሥታት የተበረከቱ ዘውዶች፣ የእጅ እና የመጾር መስቀሎች፣ አጼ ዘርዓያዕቆብ ለገዳሟ ያበረከቱት ከብረት የተሠራ የጦር ቀሚስ፣ ባርኔጣ እና የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የወርቅ ዘውድን አንስተዋል፡፡
ሌላው በገዳሙ የሚገኘው ረጅም እድሜ ያስቆጠረው የአብነት ትምህርት ቤት መኾኑን ነግረውናል፡፡ የውሉደ አርከ ስሉስ የአብነት ትምህርት ቤት በደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም ውስጥ የሚገኘው መንፈሳዊ ሀብት ነው፡፡ ደብረ ወርቅ ማርያም ቀደምት የአብነት ትምህርት ቤት ከሚገኝባቸው ገዳማት አንዷ ናት ያሉት አፈ መምህሩ በገዳሟ በአራቱ ጉባኤያት ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ጥንታዊ የኾኑት የቆሜ እና አጫብር ዜማ ትምህርቶች የሚሰጥበት መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ እንደሚያመለክተው በገዳሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው ቅርስ የአጼ አዕላፍ ሰገድ ሕንጻ ነው፡፡ ይህ ሕንጻ አጼ አዕላፍ ሰገድ (ፃድቁ ዮሐንስ) ለወይኒት መቀመጫ እንዲኾን እንዳሠሩት የሚነገርለት እና በገዳሙ ሙዚየም ከመገንባቱ በፊት ተንቀሳቃሽ ቅርሶች እቃ ቤት ኾኖ ያገለግል የነበረ በጎንደር ነገሥታት የኪነ ሕንጻ ጥበብ በድንጋይ እና በኖራ የተሠራ ባለአንድ ፎቅ ሕንጻ ነው፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ብርቄ ይዘንጋው ዞኑ በርካታ ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሠራሽ መስህብ ሀብቶች የሚገኙበት መኾኑን ገልጸዋል። ከነዚህም መካከል የደብረ ወርቅ ማርያም አንዱ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዞኑ የሚገኙ ቅርሶችን ከመንከባከብ አንጻር ቋሚ ቅርሶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው የጽዳት እና እንክብካቤ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን አንስተዋል፡፡
ተንቀሳቃሽ ቅርሶችም ለስርቆት እና ለዘረፋ እንዳይጋለጡ ቅርሶቹ በሚገኙበት የደብር ሙዚየሞች እየተገነቡ በአግባቡ ጥበቃ እየተደረገላቸው እንዲጎበኙ የማድረግ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡ የዞኑን መስህብ ሀብቶች ለቱሪዝም ገበያ እንዲውሉ ለማድረግ በወረዳዎች እና በዞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን