እድሜ ጠገቡ እና ታሪካዊው ቅርስ- ጎዜ መስጊድ

0
86

ባሕርዳር፡ ሐምሌ 18/2017ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ጥንታዊ እና ቀዳሚ ከኾኑ መስጊዶች መካከል አንደኛው እንደኾነ ይነገርለታል።

ዛሬም ድረስ ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ጎዜ መስኪድ በአማራ ክልል ምሥራቃዊ አቅጣጫ ላይ ከምትገኘው ሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋሮቢት ከተማ በቅርብ ርቀት ከሚገኙ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው።

የመስጊዱ አገልጋይ አሚን እንድሪስ እንደነገሩን ጎዜ ግድግዳና ጣሪያው በጥርብ ድንጋዮች የተሠራ እና አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ነው። ስፋቱ ሰባት ሜትር ገደማ ሲደርስ ከምድር እስከ ጣሪያዉ ደግሞ አራት ሜትር ከፍታ አለው። የመስጊዱ የውስጠኛ ክፍል ሲታይ የድንጋዩ የጣሪያ ክዳን አራት አግዳሚ ጥርብ ወራጆች በዙሪያዉ ካለዉ ከድንጋይ ካብ ጋር ተስማምተውና ላዩ ላይ አርፈው ይታያሉ፡፡ አግዳሚ ጥርብ ጣውላዎቹ በመስጊዱ መሀል በቆሙ አራት ምሰሶዎች እንዲያርፉ ተደርገዋል።

በጎዜ መስጊድ ዙሪያ ጥንታዊ የመቃብር ስፍራዎች ይገኛሉ። የዚያ ዘመን ነዋሪዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ዓመቱን ሙሉ ውኃ የማይጠፋባቸው ሁለት ጉድጓዶችም አሉ። እነዚህ የውኃ ጉድጓዶች በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ “እናትና ልጁ” የሚል መጠሪያ አላቸው። የውኃ ጉድጓዶቹ ዛሬም ድረስ አገልግሎት እየሰጡ ነው።

ጦሮች፣ አንካሴዎች፣ ኪታቦች፣ አባቶች ለመዋቢያ ይጠቀሙባቸቸው የነበሩ ቁሳቁሶች እና ይይዟቸው የነበሩ ዱላዎች በተንቀሳቃሽ ቅርስነት፣ ኪነ ሕንጻውን ደግሞ በቋሚ ቅርስነት መመዝገባቸውን አሚን እንድሪስ ነግረውናል።

በሂጅራ አቆጣጠር 111ኛ ላይ መስጊዱ ተጠናቅቆ እንዳለቀ ኪነ ሕንጻው ላይ ተጽፎ ይገኛልም ብለዋል። አንዳንዶች 6 መቶ፣ አንዳንዶች 8 መቶ ዓመት እድሜ አለው የሚሉ እንዳሉ የገለጹት አሚን እንድሪስ የሃይማኖቱ ተከታዮች ግን በሂጅራ አቆጣጠር ተጽፎ የሚገኘውን እንደሚከተሉ ነግረውናል።

መስጊዱ ከሰው ውጭ እንስሳት እንኳ የማይወጡት ሹል ተራራ ላይ የሚገኝ ነው። መስኪዱን ማየት ፈልገው መውጣት እና ቀርበው ማየት ያልቻሉ ሰዎች ፊት ለፊት በሚገኝ ደልዳላ ቦታ ላይ ኹነው ርቀቱንና የዳገቱን ክብደት በግጥም እንዲህ ይገልጹታል፦

”ጎዜ ጎዜ ቢሉኝ ጎዝጓዛ ነው ብየ”
ውኃው በቅርበታ እንጨቱ በ’የየ።

አሚን እንድሪስ እንደሚሉት ጥንታዊው ጎዜ መስጊድ ከእድሜ ጠገብነቱ የተነሳ የመስጊዱ ውስጠኛ ክፍል የመሰንጠቅና የውጭው ክፍል ደግሞ የመንሸራተት ሁኔታ ታይቶበት ነበር። ይህንን የጎዜን ጉዳት የተመለከቱ እና ታሪካዊ ይዘቱ ተጠብቆ እንዲቆይ የሚፈልጉ የአካባቢው ነዋሪዎች መልእክታቸውን በግጥም እንዲህ ሲያስተላልፋ ነበር፦

“የእነ ፈቂ አሕመድ፣ የእነ’ማየ መንደር”
ጎዜ ሊፈታ ነው ኑዛዜ ተናገር ።

የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ዳይሬክተር ጋሻዬ መለሰ እንደነገሩን መስጊዱ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እና በአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጥምረት ታሪኩን እና ይዘቱን የጠበቀ የጥገና ሲሠራለት ቆይቶ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

ባለፋት ሁለት ዓመታት አካባቢው ላይ የነበረው የጸጥታ ችግር የጥገና ሂደቱን ለሚከታተሉ ሙያተኞች አስቸጋሪ ቢኾንም አሁን ላይ ጥገናው 75 በመቶ መድረሱም ተመላክቷል።

መስጊዱ ላይ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት አሚን እንድሪስ የጥገናው ሥራ አሥቸጋሪ መኾኑን ገልጸዋል። የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ሁኔታውን በመረዳት በትጋት እየደገፈ በመሆኑ ምስጋና ይገባዋልም ብለዋል። ጥገናው ተጠናቅቆ የለቀማ፣ የአጥር እና የደረሳዎች ማረፊያ ክፋል እንደቀረውም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here