የእቴጌ ምንትዋብ አሻራ – ቸመራ ቁስቋም

0
66

ባሕር ዳር: ሐምሌ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቸመራ ደብረ ፅጌ ቁስቋም በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጣቁሳ ወረዳ ትገኛለች። ከደልጊ ከተማ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በ7 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ላይ ነው ያለችው፡፡

የቸመራ ደብረ ፅጌ ቁስቋም ከእቴጌ ምንትዋብ ታሪክ ጋር የሚያያዝ እና ከንግሥቲቷ ታሪካዊ አሻራዎች መካከል አንዷ እንደኾነችም ይገለጻል።

አመሠራረቷም ከእቴጌ ምንትዋብ ጋር የሚገናኝ መኾኑን የደብረ ፅጌ ቸመራ ማርያም አሥተዳዳሪ አባ መልዓከ ፅጌ ፍሬ ስብሀት ማህተም ያስረዳሉ።

እቴጌ ምንትዋብ ቤተክርስቲያን ለመገንባት ልዩ ፍቅር እንደነበረባቸው እና በንግሥና ዘመናቸውም በርካታ ሕንጻዎችን እና አብያተ ክርስቲያናትን እንዳሠሩ በቤተክርስቲያኗ የተገኙትን የታሪክ ድርሳናት በመጥቀስ ተናግረዋል።

እንደ አባ መልዓከ ፅጌ ፍሬ ስብሐት ገለጻ እቴጌ ምንትዋብ በንግሥና ዘመናቸው በጎንደር የምትገኘውን የደብረ ፀሐይ ቁስቋምን እንዳስገነቡ እና በኋላም ሌላ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት አይራ ወደ ምትባል ቦታ እንዳቀኑ ይገልጻሉ።

አይራ ከተባለችው ሥፍራ እንደደረሱም ቤተክርስቲያን ለማሠራት ሥራ ጀመሩ ይላሉ። ነገር ግን በወቅቱ የነበረው እና ኮሬ የተባለው የአካባቢው ገዥ ቦታውን የእኔ ነው በሚል ምክንያት የሚሠራውን ቤተ ክርስቲያን ማታ ማታ እያፈረሰ ያስቸግር እንደነበር ታሪኩን አጣቅሰዋል።

በወቅቱ በድርጊቱ የተቀየሙት እቴጌ ምንትዋብ የአካባቢውን ማኀበረስብ በማሰባሰብ ቢያወያዩም ኅብረተሰቡ ግንባታውን ማን እንደሚያፈርስው መረጃ ሊሰጧቸው አልቻሉም ነበር ነው ያሉት።

ከዚያ በኋላ “እግዚአብሔር አልፈቀደውም” በማለት ፈረሳቸውን አስጭነው ‘ቸ ምራ’ እያሉ ይጓዛሉ፤ አሁን ቤተክርስቲያኗ ከምትገኝበት ቦታ እንደደረሱ ፈረሱ ተኝቶ አልነሳም በማለቱ ከዚሁ ስፍራ እንደቆዩ ገልጸዋል።

ይህንን ተከትሎ “እንዲያውም ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ቦታ ላይ መሠራት አለበት” ብለው መወሰናቸውንና ደብሯም ቸመራ የሚል ስያሜ እንደተሰጣት ነው ያብራሩት።

በዚህም በ1724 ዓ.ም የቸመራ ደብረ ፅጌ ቁስቋም ደብርን በኖራ እና በእንቁላል ግንብ በማሠራት እንደመሠረቷት ነው የገለጹት፡፡

እቴጌ ምንትዋብ የቸመራ ቁስቋም ደብርን ከመሠረቱ በኋላ ካላቸው የመንፈሳዊ ፍቅር የተነሳ 15 የሚቀድሱ ካህናትን እና ዲያቆናትን መድበው ለሰባት ዓመታት ያህል በደብሯ አገልግሎት እንዲሰጥባት አድርገዋል ነው ያሉት።

እርሳቸው እንደሚናገሩት የገነቡትን ሕንጻ በኋላ ድርቡሾች (የሱዳን ወራሪዎች) እንዳቃጠሉት እና ሕንጻ ፍርስራሹ “የእቴጌ ምንትዋብ ቤተክርስቲያን ፍርስራሽ” እየተባለ እስከ አሁን ድረስ ቅርስ ኾኖ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የቸመራ ቁስቋም ደብሩ በአዲስ መልኩ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ቦታ በርካታ ጥንታዊ የብራና መጽሐፍት፣ መገልገያዎች እና ሌሎችም ታሪካዊ ቅርሶች የሚገኙባት መኾኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም የስንክሳር፣ የግብረ ህማም፣ የአርባዕቱ ወንጌል፣ የግንዘት መጽሐፍት እንዲኹም የነሐስና የብር መስቀሎች፤ ደወል፣ ቃጭል፣ ወዘተ በቅርስነት ተመዝግበው እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በጣቁሳ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ፈንቴ እንቢበል የቸመራ ቁስቋም ታሪካዊ የቱሪስት መሥህብ መኾኗን አመላክተዋል።

እስከ ቦታው ድረስ የመንገድ መሠረተ ልማት እንዳለም ነው የተናገሩት። ደልጊን መሠረት አድርጎ ከጎንደር እና ከባሕር ዳር በጀልባ መጓዝ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

በወረዳው ከቸመራ ደብረ ፅጌ ቁስቋም በተጨማሪ የሳር ውኃ፣ የጦር አውድማ እና የአጼ ዮሐንስ ዋርካ፣ የአጼ ቴዎድሮስ ምሽግ፣ የአረማ ፍል ውኃ እና ሌሎችም የቱሪስት መሥህቦች እንደሚገኙ አመላክተዋል።

ይህንን ታሪካዊ ቦታ ጨምሮ በወረዳው የሚገኙትን የመስህብ ሀብቶች ለማስተዋወቅ ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ነው ያነሱት።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here