ጎንደር እና አድርሽኝ

0
48
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ወረሐ ነሐሴ ሲገባ የፍልሰታ ጾም መጾም ይጀመራል። የፍልሰታ ጾም በጉጉት ትጠበቃለች። በተለይም ደግሞ ሕጻናት ይናፍቋታል።
በፍልሰታ ጾም ሕጻናት በቤተክርስቲያን አጸድ ሥር ይሰባሰባሉ። ሊቃውንት በአገልግሎት ይበረታሉ። ምዕምናን በጸሎት እና በምሕላ ይጸናሉ። በፍልሰታ ጾም ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር ሃይመኖትን መሠረት ያደረገ ማኅበራዊ ክዋኔም ይከወናል።በተለይም በጎንደር ከተማ እና አካባቢዋ፣ ከሱባኤው ጎን ለጎን የሚከወን አንድ ልዩ ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ክዋኔ አለ።ይህም አድርሽኝ ይባላል። አድርሽኝ ቅድስት ድንግል ማርያምን እያሰቡ የሚከወን ሥርዓት ነው። ማኅበራዊ መስተጋብሩ ከፍተኛ እንደኾነ ይነገራል።
የአድርሽኝ ታሪክ እና አመጣጥ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባኤያት ምክትል መምህር መምህር ዘላለም ሀዲስ እንደነገሩን አድርሽኝ የተጀመረው በ1703 ዓ.ም በአጼ ዮስጦስ ነው።ንጉሡ ወደ ሱዳን የነበረባቸውን ዘመቻ ድል አድርገው በሰላም ከተመለሱ በድንግል ማርያም ስም ውኃ እንደሚያጠጡ ተስለው ነበር።ዘመቻቸውን በድል ተወጥተው ወደ ጎንደር ሲመለሱም ወቅቱ የፍልሰታ ጾም ነበር። ንጉሡም ቃል ኪዳናቸውን ፈጸሙ። የተጠሙትን አጠጡ። በቤተ መንግሥት አካባቢ አድርሽኝ ብለው በመሰየም ይህንን ዝክር እንደጀመሩት ገልጸዋል።
የአድርሽኝ ክዋኔ እና ዓላማ
አድርሽኝ በየዓመቱ በጾመ ፍልሰታ ወቅት የሚካሄድ ሥርዓት ነው። ነዋሪዎች በየቤቱ ተሠባሥበው ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ሃይማኖታዊ ትምህርት እየተማማሩ፣ ስለ ሀገር ሰላም እየጸለዩ እና መዝሙሮችን እየዘመሩ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።በዚህ ወቅት ከጾሙ ጋር አብረው የሚሄዱ ምግቦች ቀዝቃዛ ውኃ፣ ቆሎ እና ዳቦ በጋራ ይቀርባሉ።ይህ ክዋኔ ለሁለት ሳምንታት ይቆያል፤ በ16ኛው ቀን ጾሙ ከመፈታቱ በፊት ግን አባላቱ ገንዘብ በማዋጣት ለተቸገሩ ወገኖች ጾም እንዲፈቱ የማድረግ ሥራን ይከውናሉ። ይህም ከአድርሽኝ ዋና ዓላማዎች አንዱ ነው። ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው ሥርዓት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ በመስፋፋት በዚህ ዘመን ደርሷል።
ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ጠቀሜታዎች
አድርሽኝ ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ፋይዳው ሰፊ ነው። መምህር ዘላለም እንደሚያብራሩት፣ ሰዎች ተሠባሥበው ስለ ሃይማኖታቸው የሚማሩበት፣ ስለ ሀገር የሚጸልዩበት እና በየአካባቢው እርስ በእርስ የሚተዋወቁበት አጋጣሚ ነው። በቅድስት ድንግል ማርያም ስም ዝክር የዘከረ በሃይማኖቱ ትልቅ ዋጋ ያሰጣል።ወይዘሮ እናንየ አውራሪስ የተባሉ የጎንደር ነዋሪም አድርሽኝ ስለ ማኅበራዊ ሕይወታቸው የሚመክሩበት እና በሰላም ለመቆየት የሚመራረቁበት መድረክ እንደኾነ ይናገራሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ማኅበሩ በጎ ተግባራትን ይፈጽማል። አቅመ ደካሞችን በመርዳት፣ ልብሳቸውን በማጠብ፣ ቤታቸውን በመጠገን እና የግል ንጽሕናቸውን በመጠበቅ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ያከናውናል ብለዋል።በተለይ በጾሙ ማብቂያ ላይ ገንዘብ አዋጥተው ለተቸገሩ ሰዎች ምግብ በማዘጋጀት የሚፈጽሙት እርዳታ ከፍተኛ ማኅበራዊ ፋይዳ አለው ይላሉ።
ወጣት ኤርሚያስ አሰፋም እንደተናገረው ልጆች በዚህ ባሕል ተሳትፈው እንዲያድጉ እና ተረካቢ እንዲኾኑ ይደረጋል። በሰንበት ትምህርት ቤቶችም ልጆች የራሳቸውን የአድርሽኝ መርሐ ግብር ያካሂዳሉ። አድርሽኝ በጎንደር ጥንታዊ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ እሴት ያለው ተግባር ነው። በጎንደር እና በአካባቢው ባሉ አብያተክርስቲያናትም ትምህርት እየተሰጠበት ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሠራ መኾኑም ተገልጿል። አድርሽኝ ሃይማኖት እና እሴት የሚነገርበት፣ የቆዬው የሚገለጥበት፣ በነፍስም በስጋም ሃሴት የሚደረግበት ነው።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here