ባሕር ዳር: ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጡሩሲና መስጊድ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከከሚሴ ከተማ በ16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በደዋ ጨፋ ወረዳ ሃሮ ባቄሎ ቀበሌ ይገኛል።
በምሥራቅ አማራ የጉብኝት መስመር ከሚገኙት ዋና ዋና የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች መካከልም አንዱ ነው። በአካባቢው ከሚገኙት የቱሪዝም ፀጋዎች ጋር ተዳምሮ ለቀጣናው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ይገለጻል።
በጡሩሲና መስጊድ የሚያገለግሉት እና የመስጊዱ አስተባባሪ ሼሕ አብዱልሀቅ መሐመድ መስጊዱ በመጀመሪያ በባሕላዊ መንገድ በሣርና በእንጨት የተሠራ ታሪካዊ መስጊድ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ሼክ መሐመድ አማን በተባሉ አባት እንደተመሰረተም ነው ያስረዱት፡፡ ጡሩሲና መስጊድ ለየት ያለ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚከናወንበት መስጊድ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡
ሙስሊሞች ራሳቸውን ከዓለማዊ ሕይወት ሙሉ በሙሉ አግልለው መንፈሳዊ ተግባራትን በማከናወን ብቻ የሚኖርበት መሥጊድ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ሴትና ወንድ የእምነቱ ተከታዮች ለየብቻ ከማንም ጋር ሳይገናኙ በጾምና በዱዓ፣ በሃይማኖታዊ ትምህርት፣ ጽሑፎችን እና ክታቦችን በማዘጋጀት፣ በመንፈሳዊ ሕይወት ይኖሩበታል ብለዋል።
እርሳቸው እንደገለጹት በመስጊዱ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡ ለአብነትም ቡና ቤት፣ የማር (ብርዝ) ቤት፣ የስጋ ቤት፣ የምግብ ማብሰያ ቤት እና የዕቃ ቤት ተዘጋጅተው መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በእነዚህ ቤቶችም ከድሮ ጀምሮ የኖሩ ትላልቅ ጀበናዎች፣ የቡና መውቀጫዎች፣ ከአንድ እንጨት የተፈለፈሉ ትላልቅ ገንዳዎች፣ ከ180 በላይ ስኒዎችን መያዝ የሚችል ረከቦት እና ሌሎች በርካታ ባሕላዊ የመገልገያ ዕቃዎች እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመምጣት ብዙዎች የመውሊድ በዓልን በጡሩሲና እንደሚያከብሩም ነው የተናገሩት።
በደዋ ጨፋ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ባለሙያ መሐመድ አሊ መስጊዱ በ1960 ዓ.ም እንደተመሰረተ ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ በሚታወቅበት ጥበብ እና ባሕላዊ አሠራር የተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ታሪካዊ ከመኾኑ ባሻገር የተለየ ዕሴት እንዳለውም ይናገራሉ። መስጊዱ “ሀሪማ” የተባለ ልዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚከናወንበት ነው ብለዋል።
በግቢው ውስጥ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚከናወንበት የሴቶች እና የወንዶች መስጊዶች ለየብቻ ተለይተው መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
በ2009 ዓ.ም የመብረቅ አደጋ ደርሶበት ተቃጥሎ የነበረ መኾኑን ያስታወሱት ባለሙያው በማኅበረሰቡ እና በመንግሥት ድጋፍ እንደገና ጥንታዊ አሠራሩን በጠበቀ መንገድ መሠራቱን ነው የገለጹት።
የጡርሲና መስጊድ በወረዳው አንዱ የቱሪዝም መዳረሻ መኾኑንም ገልጸዋል። በጎብኝዎች እንዲጎበኝ የመንገድ፣ የውኃና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር ጋሻዬ መለሰ የጡርሲና መስጊድ በቅርስነት የተመዘገበ ቋሚ ቅርስ መኾኑን ገልጸዋል።
መሥጊዱ ጉዳት ከደረሰበት በኋላም ቢሮው ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ቅርስነቱን በጠበቀ መልኩ መልሶ እንዲገነባ ማደረጉን አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን