ወልድያ፡ ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸንድዬ እና የሶለል በዓል ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የሰሜን ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ገነት ሙሉጌታ የአሸንድዬ እና ሶለል በዓል ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር በላስታ፣ በግዳን፣ በላሊበላ፣ በመቄት፣ በየጁ እና በራያ አካባቢ ሕዝባዊ በዓል መኾኑን ገልጸዋል። በቆቦ እና በላሊበላ ከተማ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በዞን ደረጃ እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገም ነው ብለዋል።በተለይም በቆቦ ከተማ የሚከበረው በዓል ሁሉንም የራያ ወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮች ያሳትፋል ነው ያሉት።
በዓሉ ትውፊቱን ሳይለቅ ለትውልድ እንዲሻገር ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ኀላፊዋ አስረድተዋል። በበዓሉ ለመታደም የሚፈልጉ የሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ ሀገር እንግዶችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል። ኀላፊዋ በዓሉ በሚከበርባቸው አካባቢዎች እንግዶች እንዲታደሙ እና ከሰሜን ወሎ ሕዝብ ጋር በጋራ ያሳልፉ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!