ሻደይ የአንድነት እና የመከባበር ማሳያ በዓል ነው።

0
35
ሰቆጣ፦ ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሻደይ በዓል በሰቆጣ ከተማ “ዝክረ ሌተናል ጄኔራል ኃይሉ ከበደ” በሚል መሪ መልዕክት እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ ሻደይ ለዘመናት የኖረ የዋግ ሹሞች ቱባ ባሕል ነው ብለዋል። የሻደይ ቄጤማ ሰላምን የሚሰብክ የአንድነት ማኅተም ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ዛሬም ሻደይ በሰላማዊቷ ከተማ ሰቆጣ ሰላሙን ጠብቆ በአንድነት እና በፍቅር መከበሩ የሻደይ በዓል የሰላም በዓል መኾኑ ማሳያ ነው ብለዋል። የሰቆጣ ከተማ የብረት ማዕድን፣ የከበሩ ድንጋዮች እና የሴራሚክ ማዕድን ያሏት ከተማ ናት ያሉት አቶ ጌትነት እሸቱ ሰላሟ በጸናባት ሰቆጣ ከተማ መጥተው መዋለ ንዋያቸውን ለሚያፈስሱ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
የሻደይ በዓል በዋግ ኽምራ ሲከበር ኅብረ ብሔራዊነትን በሚገልጥ መልኩ እየተከበረ መኾኑን የገለጹት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ኢዮብ ዘውዴ ናቸው። ሻደይ ለዘመናት የሴቶችን አንድነት እያጠናከረ የመጣ የሴቶች የነጻነት ቀን እንደኾነ ያወሱት አቶ ኢዮብ በዩኒስኮ እንዲመዘገብ ከአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በትብብር እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል። ይህንን የአንድነት እና የመከባበር በዓል በመፈቃቀር ብሎም የብሔረሰብ አሥተዳደሩን ሰላም በማጽናት ማክበር እንደሚገባም አሳስበዋል። የሻደይን በዓል ከነሐሴ 16/2017 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም ድረስ መከበሩ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here