ሰቆጣ: ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሻደይ በዓል በሰቆጣ ከተማ በድምቀት መከበሩን ቀጥሏል።
የሻደይ በዓልን ሴቶች ያለከልካይ የባሕል ጨዋታቸውን ያቀርቡበታል፤ በባሕላዊ አልባሳት ደምቀው ይቦርቁበታል። የሻደይ በዓልን ለማክበር ከመጡት መካከል የድሃና ወረዳዋ የሻደይ ተጫዋች አስቴር ካሳ “ሻደይ ነጻነታችን የታወጀበት የአብሮነታችን ቀን ነው” ብላለች። ሻደይ የሴቶችን እኩልነት ያረጋገጠ እና የሴቶችን ውበት የገለጠ ቀን ነው ያለችው ደግሞ የስሃላ ሰየምት ወረዳ የሻደይ ተጫዋቿ ምግብ ዓለምነው ናት። ሻደይን በሰቆጣ ከተማ በነጻነት በማክበሯ መደሰቷንም ገልጻለች።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ወጣት ዘውድ ሰፊው በበኩሏ የጻግቭጂ ወረዳን ወክላ ስትሳተፍ የመጀመሪያዋ እንደኾነ ገልጻ ባለፉት ዓመታት በወረዳዋ ከጓደኞቿ ጋር እያከበረች እንዳደገች ጠቁማለች። ከመላው የዋግ ቆነጃጅቶች ጋር በነጻነት ባሕሏን መግለጿንም ነግራናለች። የሻደይ በዓል ለሴቶች ነጻነትን ያጎናጸፈ ባሕላዊ ጨዋታ ብቻ ሳይኾን ለመላው የዋግ ሕዝብ ታሪክ በውስጡ የያዘ ሊነበብ የሚገባው መጽሐፍ ነው ያሉት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ ናቸው። “ሻደይን ቀደምት እናቶቻችን ጠብቀው ከነሙሉ ክብሩ ለእኛ እንዳወረሱን ሁሉ እኛም ጠብቀን ባሕሉን ሳንበርዝ እና ሳንቀላቅል ለተተኪ ልጆቻችን ማውረስ ይገባናል” ብለዋል አቶ ኃይሉ። የሻደይ ባሕላዊ ጨዋታ በሰቆጣ ከተማ ለሁለተኛ ቀን እየተከበረ ነው። የወይዘሪት ሻደይ የቁንጅና ውድድርም ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን