ባሕርዳር፡ ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ ነዋሪ እና አስጎብኝ ብርሃኑ አበበ በከተማዋ ብዙ ዋርካዎች መኖራቸውን ጠቅሰው የጃንተከል ዋርካ ግን አጼ ፋሲለደስ ከመንገሣቸው በፊት የነበረ እና ታሪካዊ ሁነቶች የተካሄዱበት መኾኑን ገልጸውልናል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ቦታው የተለያዩ ሁነቶች የተከናወኑበት ነው ብለውናል። ከተከወኑ የታሪክ ሁነቶች መካከልም ለአካባቢው ምጥ ሆኖ የነበረው የአጼ በካፋ እና የእትጌ ምንትዋብ ወንድ ልጅ መወለድ እና የንግሥና ማስቀጠል መረጃ በቦታው መነገርን ከታሪኮች ውስጥ መዘው አጋርተውናል።
ጃን ተከል አበርክቶው ብዙ ነው። ገጣሚው ቢገጥምለት፣ ደራሲው የድርሰቱ አንጓ ቢያደርገው፣ ሊቃውንቱ ቢያወድሱት፣ ዜመኞች ቢያዜሙለት፣ አዕዋፋት ዝማሪያቸውን ቢያንቆረቁሩለት ያንሰዋል ቢባል ማጋነን አይኾንም።
“በኳሊ በር አ’ርጎ ጃንተከል ዋርካው፣
ሲደክሙ ‘ሚያርፉበት ትዝ አለኝ ጥላው”
እየተባለም በማኅበረሰቡ ክዋኔዎች በሥነ ቃል እንደሚዜምለት ሀሳብ ሰጫችን ብርሃኑ አበበ ነግረውናል።
በቀጣይ ቦታው ንጉሣዊ እራት ግብዣ የሚካሄድበት፣ የንጉሣውያን ወንበሮች ተቀምጠው የፎቶ አገልግሎት መስጫ ኾኖ የሚያገለግልበት፤ ማንበቢያ ቦታ የሚኾንበት፣ ቴዓትሮች የሚካሄዱበት ቢኾን በማለት ግላዊ አስተያየታቸውንም ጠቁመዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አይቸው አዲሱ ጃንተከል ዋርካ ከአጼ ፋሲል በኋላ የተነሱ ነገሥታት ሲሾሙ እና ሲሻሩ “ያለንም እኛ፣ የሞትንም እኛ ሕዝብ ተስማማ” ብለው ሹመታቸውን የሚያወጁበት እና የሚሽሩበት ቦታ እንደነበር ጠቅሰዋል።
አዋጅ ይነገርበት፣ የእርቅ እና ሽምግልና ሥርዓት ይከወንበት፣ ፍርድ ይሰጥበት ነበርም ብለዋል። በጻድቁ ዮሐንስ ወይም አዕላፍ ሰገድ ዮሐንስ ጊዜ በጉስቁልናው ከባለቤቱ የተባረረ አህያ የጃንተከልን በር በማንኳኳቱ ባለቤቱ ተጠርቶ እንዲንከባከበው የተደረገበት ነው ያሉት አቶ አይቸው ይህም የእንስሳት መብት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረበት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይገልጣሉም ብለውናል።
ጃንተከል የደከመው ማረፊያ፣ መዘከሪያ፣ የሰዎች መገናኛ፣ ዝምድና መጠያየቂያ፣ ስለሀገር የሚመከርበት እና ማኅበራዊ ሚዲያ ከመምጣቱ በፊት መረጃ ማግኛ ነው ብለዋል። ንጉሡም ከጦር አበጋዞቻቸው እና ዘመዶቻቸው ጋር ቦታው ላይ ይመክሩበት እና ይዘክሩበት እንደነበርም ነው የነገሩን።
“ጃን ተከል” ማለት በንጉሥ የተተከለ የሚል ትርጉም እንዳለውም ገልጸውልናል ባለሙያው። ነገር ግን ንጉሡ አጼ ፋሲል ቤተ መንግሥታቸውን እስከሚሠሩ ድረስ ድንኳን ጥለው ለአራት ዓመት በማረፊያነት ተጠቅመውታል እንጂ አልተከሉትም ሲሉ አቶ አይቸው ነግረውናል። የታሪክ አስረጅዎች እንደሚያስረዱትም ቤተ መንግሥቱ ከተገነባበት ከ1628 ዓ.ም 100 ዓመት ቀደም ብሎ የነበረ ዋርካ ነው። በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ለንጉሡ ከሰጧቸው ትኩረት በመነሳት ለንጉሡ ያላቸውን ክብር ለመግለጽ ከሌሎች ዋርካዎች በተለየ ስም እንዳወጡለትም ገልጸዋል።
የአጼ ፋሲል ግንብ እድሜ 400 ዓመት አካባቢ ተጠግቷል፤ ስለዚህ ጃንተከል 500 ዓመት እድሜ እያስቆጠረ መኾኑን ገልጸውልናል።
ጃን ተከል ዋርካ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ትውፊት እና ከዛም በላይ የኾነ ዘመን ተሻጋሪ ውርስ እንደኾነ የጠቀሱት ባለሙያው እርሱን በሚመጥን እና በሚያሳይ መልኩ እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!