በዓመት አንድ ጊዜ የሚከወነው ገበያ እና ታሪኮቹ

0
8
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ጌራ ምድር ወረዳ የሚገኘው ምስሐለ ማርያም በጥንታዊ ታሪኩ፣ በባሕላዊ እሴቶቹ እና ልዩ በኾነው የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል አከባበር የሚታወቅ ልዩ ስፍራ ነው።
ይህ ቦታ ከመሐል ሜዳ ከተማ በ13 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲኾን የነገሥታት ታሪካዊ አሻራ ያረፈበት እንደኾነ ይነገራል።
👉ታሪካዊ አመጣጥ
የቦታው ታሪክ ከአጼ አምደ ጽዮን ዘመን ጋር የሚያያዝ ነው። ንጉሡ በዚህ ስፍራ ቤተ መቅደስ ገንብተው “ማርያምን የምለምንበት” የሚል ትርጉም ያለውን “ምስሐለ ማርያም” የሚል ስያሜ እንደሰጡት ይነገራል።
👉ልዩ የገበያ ሥርዓት እና ትንብያው
በየዓመቱ ጳጉሜ 3 ቀን በሚከበረው የቅዱስ ሩፋኤል ንግሥ በዓል ላይ አንድ ልዩ የገበያ ሥርዓት ይካሄዳል።
የመንዝ ጌራ ምድር ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማህሌት ዓላማው ለአሚኮ እንዳሉት በዚህ ቀን ለገበያ የቀረቡ የቁም እንስሳት እና የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦች ዋጋ ለቀጣዩ ዓመት የኑሮ ሁኔታ ትንብያ ያገለግላል።
የገበያ እቃ ዋጋ ከጨመረ ለቀጣዩ ዓመት የኑሮ ውድነት እንደሚኖር ይተነበያል፤ ከቀነሰ ደግሞ ዓመቱ የኑሮ ውድነቱ የተሻለ እንደሚኾን ይታመናል ነው ያሉት።
ይህንን ትንበያ ቀደምት ነገሥታት ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያገለግል አድርገው ይጠቀሙበት እንደነበር ይነገራል።
👉ባሕላዊ የጋብቻ ሥርዓት
ቀደም ሲል በዚህ ዓመታዊ ገበያ ላይ ወጣት ወንዶች እና ልጃገረዶች ይተጫጩ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ሚስት የሚፈልግ ወጣት ራሱን አስውቦ ወደ ገበያው ይወጣል፤ ባል የምትፈልግ ሴት በእጅ የተሠሩ እንደ ሰፌድ፣ ሌማት፣ እንቅብ እና የሸክላ እቃዎችን ይዛ ትወጣለች።
ወጣቱ ሴቷን አይቶ ካጫወታት እና ከወደዳት ለትዳር ይጠይቃታል፤ ሴቷም ወጣቱን ከወደደችው ተስማምታ ትዳር እንደሚመሰርቱ ይስማማሉ።
👉የዝናቡ ጸበል
በበዓሉ ዕለት ዝናብ ቢዘንብ፣ ማንም ሰው ጃንጥላ ዘርግቶ ራሱን አይከላከልም፤ ይልቁንም ዝናቡ እንዲመታው ተስተካክሎ ይቆማል፤ ምክንያቱም ዝናቡ በዓመት አንድ ጊዜ የሚገኝ “ድንቅ ጸበል” እንደኾነ ስለሚታመን ነው።
ይህ ስፍራ ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር ታሪካዊ፣ ባሕላዊ እና ማራኪ ገጽታዎች ያሉት በመኾኑ ለጥናት እና ምርምር፣ ለቱሪዝም መስህብነት ከፍተኛ እምቅ አቅም እንዳለውም ተናግረዋል።
የመንዝ ጌራ ምድር ነዋሪው ዘበነ ግዛው በዚህ ታሪካዊ የገበያ ቦታ እየሄዱ እንደሚገበዩ ገልጸዋል።
ገበያው ላይ ይሄ ቀረ የሚባል አገልግሉት እንደሌለ ለአሚኮ ተናግረዋል።
ሁሉም ነገር በአንድ ላይ የሚገኝበት ውብ እና ማራኪ ስፍራ ነው ብለዋል። ይህን ታሪካዊ ገበያ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በጉጉት የሚጠብቀው መኾኑን ገልጸዋል።
በገበያው ላይ ያልታዩ አዳዲስ ነገሮችም ብቅ ብቅ እንደሚሉ እና ረዘም ላለ ጊዜ የተጠፋፉም ሰዎች ገበያው ላይ የሚገናኙበት በመኾኑ በጉጉት የሚጠበቅ ቀን ነው ብለዋል። የግብይት ሥርዓቱ ቢጠና የቀደመውን እሴት እና ታሪክ ለማጉላት እንደሚያስችል ተናግረዋል። በተለይም በገበያው የሚደረገው ትንቢያ አዲስ ነገር ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here