የከሴ አጨዳ እና የእንግጫ ነቀላ ባሕላዊ ክዋኔው መንፈሳዊ ይዘትም ያለው ነው።

0
4
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ በዓል በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች በድምቀት ሲከበር የኖረ በዓል ነው፡፡
በያዝነው ዓመትም በዓሉን በድምቀት እያከበሩ መኾናቸውን የተናገሩት የባሶሊበን ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቋሚ ቅርስ ምዝገባ ባለሙያው ተስፋው ገበየሁ ናቸው፡፡
በዓሉን ለማክበር ቀደም ብለው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ የቆዩ መኾኑን ነው የገለጹት። በዓሉ በየጁቤ ከተማም በድምቀት ይከበራል ነው ያሉ፡፡
ይህ በዓል በአብዛኛው ሕጻናት፣ ወጣቶች እና ልጃገረዶች የሚሳተፉባቸው እና የእነሱ የመጫዎቻ፣ የመደሰቻ፣ የማመስገኛ እና የነጻነት ጊዜያቸው እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡ገ
በዓሉ በባሶሊበን ወረዳ የተለያዩ የሥራ ኀላፊዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የባሕል አምባሳደሮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት በድምቀት እየተከበረ ነው ብለዋል፡፡
መልዓከ ሰይፍ መልካም መንግሥት በምሥራቅ ጓጃም ዞን የባሶ ሊበን ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አሥኪያጅ እና የየጁቤ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አሥተዳዳሪ ናቸው። የከሴ አጨዳ እና የእንግጫ ነቀላ ባሕላዊ ክዋኔው መንፈሳዊ ይዘት ያለው እንደኾነም ነው የገለጹት። በኖህ ዘመን ምድር በንፍር ውኃ ጠፍታ በነበረበት ወቅት ኖህ እርግብን ወደ ምድር ላከ ይላል ታሪኩ ብለዋል።
እርግቧም የጥፋት ውኃ መጉደሉን ለማብሰር ከመሬት የበቀለውን ለምለም ቄጤማ በመያዝ ወደ ኖህ በመመለስ የምስራች ማብሰሯን የምናስብበት ምሳሌ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ይህንንም ምሳሌ በማድረግ እርግቧ ለምለም ቄጤማ በአፏ ይዛ የጥፋት ውኃ መጉደሉን እንዳበሰረች ሁሉ ልጃገረዶቹ እንግጫ በመንቀል እና ከሴ በማጨድ በየዘመዶቻቸው እና በየጎረቤቶቻቸው ቤት በመሄድ እንኳን አደረሳችሁ በማለት ያበስራሉ ነው ያሉት።
ይህም የክረምቱን ወቅት እና የጨለማውን ጊዜ ወጥተን ከበጋው ደረስን በማለት ዘመን መለወጡን፣ የጨለማው ጊዜ ማለፉን እና በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ መኖሩን የሚያበስሩበት ምሳሌ ነው ብለውናል።
ባሕል በሰው ልጅ የረጅም ዘመን ታሪክ ውስጥ ተፈጥሮን ለመረዳት፣ ለመቆጣጠር፣ ለማሥተዳደር፣ ለማስቀጠል እና የራሱን ህልውና ለማረጋገጥ በሰው ልጆች እና በተፈጥሮ በሚደረገው ትግል ከሰው ወደ ሰው የሚሸጋገር እና እየተሸጋገረ ያለ፣ የሚኖር ቁሳዊ እና መንፈሳዊ የቅርሶች ስብስብ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቅርሶች ጥናት ባለሙያ ነህምያ አቤ ናቸው።
ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትውፊቶች በስፋት የሚከወኑባት ሀገር ናት ብለዋል ባለሙያው።
ከእነዚህ ባሕላዊ ሃብቶቻችን መካከልም ቡሄ፣ አሸንድየ፣ ከሴ አጨዳ፣ እንግጫ ነቀላ እና በዓባይ ወንዝ ላይ የሚከበረው የዓባይ ሩፋኤል በዓላት ዋና ዋናዎቹ እንደኾኑም አብራርተዋል፡፡
በክልላችን ነሐሴን እና ጳጉሜን የማይዳሰሱ የበዓላት ወቅት በማለት ብንጠራቸው ማጋነን አይኾንም ነው ያሉት ባለሙያው። አንገታቸውን ደፍተው የሚኖሩ ልጃገረዶች በዓደባባይ ወጥተው ከከንፈር ወዳጆቻቸው እና ለትዳር አጋር ከሚኾናቸው ጋር የሚገናኙበት፣ የወደዱትን የሚያሞግሱበት፣ አምላካቸውን የሚያወድሱበት የነጻነት ጊዜያቶቻቸው ናቸው ብለዋል፡፡
በዓላቱ ትውፊታቸውን ይዘው እንዲከበሩ እና እንዳይጠፉ አክብሮ እና አስጠብቆ ለማቆየት ቢሮው ሰፊ ሥራ እያከናወነ መኾኑንም ባለሙያው ገልጸዋል።
ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ጥናት በማካሄድ፣ የፓናል ውይይት በማድረግ እና ሲምፖዚየም በማዘጋጀት በዓደባባይ ጎልተው እንዲወጡ እና በትውልዱ ውስጥ እንዲሰርጹ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here