ባሕር ዳር: መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን የዋሻ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በብዛት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ ጊዜያት የተሠሩ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ
ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሙሴ ወይም አባ ሚናስ በርካታ የአለት ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን በመሥራት ይታወቃሉ፡፡ በሰሜን ወሎ ዞን ዳውንት ወረዳ ብቻ 12 የሚደርሱ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል 1 ሺህ 600 ዓመታትን ያስቆጠረው የድባ መቅደሰ ማርያም አቡነ ሙሴ አንድነት ገዳም አንደኛው ነው፡፡ ገዳሙ በሰሜን ወሎ ዞን ዳውንት ወረዳ ከወረዳው ዋና ከተማ ኩርባ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተሠራ ይነገራል፡፡
ከገዳሙ ለመድረስ ከመኪና ወርደው ወደ ገዳሙ ለመድረስ ቁልቁለታማውን የ30 ደቂቃ መንገድ መሔድ ግድ ይላል፡፡ ገዳሙ የአንድነት ገዳም ነው። በውስጡ 150 የሚደርሱ መነኮሳት እንደሚኖሩ ይነገራል፡፡ እነዚህ መነኮሳት በምናኔ ኑሯቸው በገዳሙ ውስጥ የግብርና ሥራዎችን ያከናውናሉ፤ በተለይም አካባቢው ለንብ ማነብ ምቹ በመኾኑ ማር ይመረታል፤ ከገዳሙ የደረሰ ማር ሳይቀምስ አይመለስም።
የድባ መቅደሰ ማርያም አቡነ ሙሴ አንድነት ገዳም ወደ ቁልቁለቱ ካልወረዱ በቀር ከላይ አይታይም፡፡ ቁልቁለቱን ከወረዱ በኋላ ከነጭ ገሃ የድንጋይ ቋጥኝ የተፈለፈለው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡
የገዳሙ አበምኔት ቆሞስ አባ ዮሴፍ ድንበሩ ቤተ መቅደሱን ልዩ የሚያደርገው ምንም አንኳን ሌሎች በሮች ቢኖሩትም በአንድ ጠባብ በር በመግባት በውስጡም ሁለቱን ቅኔ ማህሌት እና ሰባቱን ቤተ መቅደሶች ማግኘት የሚቻል በመኾኑ ነው ይላሉ፡፡ እነዚህ ቤተ መቅደሶችም የድንግል ማርያም፣ የአቡነ ሙሴ ወይም አባ ሚናስ፣ የቅዱስ ገብርኤል፣ የቅዱስ ሚካኤል፣ የመድኃኔዓለም፣ የኪዳነ ምህረት እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡
ገዳሙ ውስጡ 51 ሜትር ርዝመት፣ 26 ሜትር ወርድ ስፋት እና በአማካይ 3 ነጥብ 9 ሜትር የሚድረስ ከፍታ ያለው ነው። 27 ቋሚ አምዶችም አሉት። አምዶቹ ባለ አራት እና ባለ ስድስት ገጾች ናቸው። ኪነ ሕንጻው የተለየ እና በቀደመው ጊዜ የነበረውን የአለት ፍልፍል አሠራር የሚያሳይ ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ የውስጥ ክፍሎች ከ360 በላይ የተለያዩ የግድግዳ ላይ ቅዱሳት ስዕሎች ያሸበረቀ ነው። ሥዕሎቹም በተለያዩ ቀለሞች የተጌጡ መኾናቸውን ከወረዳው ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ሥዕሎቹ ግድግዳ ላይ ብቻ ሳይኾን በጣሪያው ላይም ይገኛሉ። በተለይም በቤተ ማርያም፣ በቤተ ሚካኤል፣ በቤተ ገብርኤል እና በቤተ ጊዮርጊስ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ ስዕሎች ይገኛሉ። ዛሬም ድረስ ከእነ ውበታቸው ይታያሉ።
የድባ መቅደሰ ማርያም አቡነ ሙሴ ፍልፍል የዋሻ ውስጥ ሕንጻ በውስጡ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎችን የያዘ ነው፡፡
የመጀመሪያው የቤተ ጊዮርጊስ ፍልፍል ሕንጻ ነው፡፡ 16 ሜትር ርዝመት እና 10 ሜትር ወርድ ያለው ነው፡፡ ወደ ቤተ ጊዮርጊስ መግቢያ ላይ ሁለት የውጭ በሮች እና አራት ማዕዘን የኾነ አንድ መስኮት ይገኛል፡፡ ሕንጻው ሦስት ክፍሎች አሉት። ቅኔ ማሕሌት፣ ቅድስት እና ቤተ መቅደስ ክፍሎች። የቅዱስ ጊዮርጊስ መንበርም ይገኝበታል፡፡
በሕንጻው ውስጥ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላቸዉ አራት አምዶችም አሉት፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የቤተ ማርያም ፍልፍል ሕንጻ ነው፡፡ ይህም ሦስቱ የቤተ ክርስቲያን ክፍሎችን የያዘ ነው፡፡ በቤተ ማርያም ቅኔ ማሕሌት ውስጥ ስድስት ቤተ መቅደሶች ይገኛሉ፡፡ እነሱም የመድኃኔዓለም፣ የአቡነ ሙሴ ወይም አባ ሚናስ፣ የቅዱስ ሚካኤል ፣ የቅድስት ድንግል ማርያም፣ የቅዱስ ገብርኤል እና የኪዳነ ምሕረት ቤተ መቅደሶች ይገኛሉ፡፡
በአቡነ ሙሴ ቤተ መቅደስ ውስጥ ጥንታዊ የድንጋይ መንበር፣ የአቡነ ሙሴ መካነ መቃብር እና በጣሪያው ላይ ደግሞ ክብ ቅርጽ ኾነው የተፈለፈሉ ሁለት የድንጋይ ጉልላቶች ይገኛሉ፡፡ ሕንጻው ርዝመቱ 21ሜትር ፣ ወርዱ ደግሞ 26 ሜትር ነው። የጣሪያው አማካኝ ቁመት 5 ነጥብ 8 ሜትር እንደኾነም ይነገራል፡፡
የቤተ ማርያም ፍልፍል አራት የውጭ በሮች እና አራት ማዕዘን የኾነ አንድ መስኮት አለው፡፡ በሕንጻው ውስጥ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላቸው 16 አምዶች አሉት። ሰባቱ አምዶች የመስቀል ቅርጽ ያላቸው ናቸው፡፡
ሌላው የሚገርመው የቤተክርስቲያኑ ክፍል ደግሞ አጽመ ቅዱሳን ክፍል ነው፡፡ ይህ ህንጻ የቅዱሳን አጽም የሚገኝበት ነው። በሁለቱ ቅኔ ማሕሌቶች መካከል የሚገኝና 14 ሜትር ርዝማኔ ያለው ክፍል መኾኑን የጽሕፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡
ከእነዚህ ክፍሎች በተጨማሪ በዋሻው ውስጥ ቤተልሔም እና ለቤተ ክርስቲያኑ መገልገያ ንዋየ ቅዱሳት እና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች የሚቀመጡበት ዕቃ ቤት ክፍል መኖሩን የገዳሙ አበምኔት ቆሞስ አባ ዮሴፍ ድንበሩ ነግረውናል፡፡
ከቋሚ ቅርሱ በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያኑ በርካታ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ከ70 በላይ የተለያዩ ብራና መጻሕፍት፣ የአቡነ ሙሴ መቋሚያ እና አክሊሎች አሉ። እንደ አበ ምኔቱ ገለጻ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን በደብር ሙዚየም አደራጅቶ ለመጠበቅ እና ለጉብኝት ለማዋል ሙዚየም እየተገነባ ነው።
ቋሚ ቅርሱን በተመለከተ ከዕድሜ ብዛት አለቱ የመሰንጠቅ አደጋ አጋጥሞታል ነው ያሉት። በተጨማሪም ቦታው ጋራ ስር ያለ በመኾኑ ናዳ በተደጋጋሚ ስለሚያጠቃው በፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እና በክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ በተገኘ 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እና በማኅበረሰብ ተሳትፎ የጥበቃ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
አሁንም ግን መሠራት ያለበት የጥበቃ ሥራ መኖሩን አንስተዋል። ለዚህ እና ለሙዚየም ግንባታው የሚመለከታቸው አካላት እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የዳውንት ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ተስፋ ሞገስ የየድባ መቅደሰ ማርያም አቡነ ሙሴ አንድነት ገዳም በርካታ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች የሚጎበኙት ጥንታዊ ገዳም ነው ብለዋል፡፡
በተለይም በሦስቱ ዓመታዊ ክብረ በዓላት በመስከረም 4 የአቡነ ሙሴ የእረፍት ቀን፣ በታኅሣሥ 8 ቀን በተወለዱበት እና ጥር 21 ቀን በአስተርዮ በዓል በአንድ ቀን ንግሥ እስከ 60 ሺህ የሚደርሱ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ የሃይማኖት ተከታዮች እንደሚታደሙ ገልጸዋል፡፡
ቦታው ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!