ባሕር ዳር፡ መስከረም 18 /2018 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ እንቁ ባህሪ ወይዛዝርት ኪዳነ ምህረት በአማራ ክልል ከሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎች መካከል አንዷ ናት።
የጎንጅ ቆለላ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበበ አዝመራው የደብረ እንቁ ባህሪ ወይዛዝርት ኪዳነ ምህረት ገዳም ከክልሉ ርዕሰ ከተማ ባሕር ዳር እስከ ጎንጅ ቆለላ ወረዳ ከተማ አዲስ ዓለም እስከተባለው ቦታ 69 ኪሎ ሜትር፣ ከወረዳው ከተማ 7 ኪሎ ሜትር፣ በጥቅሉ 76 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደምትገኝ ነግረውናል።
በ1624 ዓ.ም በአጼ ፋሲል ልጅ ንግሥት ሰብለወንጌል እንደተመሠረተች የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቅሳሉ ብለዋል። በወረዳው ባሕል እና ቱሪዝም የተመዘገቡ ቅርሶች ያሉባት መኾኗንም ጠቅሰዋል።
አቀማመጣቸው ግን ለጎብኝዎች አመቺ እንዳልኾነ አንስተዋል። ገዳሟ ታሪካዊ እና ቀደምት በመኾኗ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ጉዳት እንደደረሰባት ገልጸዋል። የፌዴራል እና የአማራ ክልል ባሕል ቱሪዝም ቢሮ በጀት በመመደብ የጥገና ሥራ እንደተሠራላትም አንስተዋል።
ቀደም ባሉት ዓመታት የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች በብዛት ይጎበኟት እንደነበር ነግረውናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የጎብኝዎች እንቅስቃሴ አለመኖሩን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት የገዳማት መምሪያ ኀላፊ መላከ ምህረት ቆሞስ አባ ጌታቸው ሙሉ ደብረ እንቁ ባህሪ ወይዛዝርት ኪዳነ ምህረት በአጼ ፋሲል ልጅ በንግሥት ሰብለወንጌል እና በባለቤቷ ደጅአዝማች ዲሜጥሮስ መሠራቷን ገልጸዋል።
ንግሥቷ ከጎንደር ወደ ጎጃም የመሄዷ ምክንያት የአባቷ የአጼ ፋሲል አያት የእቴጌ ሐመልማላዊት መኖሪያ በመኾኑ እና የአካባቢውን ባላባት ደጃዝማች ዴሜጥሮስን በማግባቷ መኾኑን ነግረውናል።
የመጀመሪያ መኖሪያዋን አድርጋ የነበረውም አሁንም በገዳሟ ቅርብ ርቀት በሚገኘው ገረገራ ፍርስራሽ ቤተመንግሥት ላይ መኾኑን ጠቅሰዋል። በኋላ ግን ወደ ወይዛዝርት ሄደዋል ነው ያሉን።
የገዳሟ የመጀመሪያ መጠሪያ ደብረ እንቁ ባህርይ ቆለላ ኪዳነምህረት እና ሁለተኛው ስሟ ደግሞ ወይዛዝርት ኪዳነ ምህረት መኾኑን ጠቅሰውልናል። ሁለተኛው ስም የንግሥት ሰብለ ወንጌል ሴት ልጆች ያስተዳድሯት ስለነበር የተሰጣት ስም እንደነበር ገልጸዋል።
የገዳሟ የግንባታ ሥራ በ1650 ዓ.ም ተጀምሮ በ1962 ዓ.ም መጠናቀቁን ጠቅሰዋል። የገዳሟ አሠራር እንደ ጎንደር ኪነ-ህንጻ መኾኑን ጠቅሰዋል። በድንጋይ እና በኖራ መሠራቱንም ነግረውናል። የሚለየው ገዳሟ ቅብ በመኾኗ ነው፤ የዕቃ ቤቱ ቅርጽ እና አሠራር ግን ተመሳሳይ ነው ብለዋል።
የገዳሟ የስዕል አሳሳል ጥበብ ከደብረ ሲና ጎርጎራ እና ከቆማ ፋሲለደስ ጋር እንደሚመሳሰልም ነግረውናል።
የገዳሟ ጣራ በቆዳ፣ በነጭ ገመድ እና ጨባ በተባለ እንጨት በቀለም አጊጦ እንደተሠራም ገልጸውልናል። እንጨቶች ያልተዛነፈ ክብ እና ተመጣጣኝ ውፍረት፣ ሲታዩ ጥርብ ድንጋይ የሚመስሉ፣ ሲዳሰሱም ልስላሴያቸው እንጨት የማይመስሉ ናቸው ብለዋል። ገዳሟን ጻድቁ ዮሐንስ ወደ ቦታው ሂደው ሲመርቁም አሁን የምትጠራበትን ስያሜ እንደሰየሟት ነግረውናል።
በገዳሟ የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች አሉ ያሉት ቆሞስ አባ ጌታቸው መጽሐፈ ሄኖክ ያለበት ደቂቀ ነብያት የሚባል ብዙ ቦታ የማይገኝ መጽሐፍ፣ ስንክሳር፣ ሃይማኖተ አበው፣ ገብረ ህማማት፣ ከነሐስ እና ከብር የተሠሩ መስቀሎች እና ቁጥራቸው በርካታ መጽሐፎች በጥራት ይገኛሉ ነው ያሉት።
የአጼ ፋሲል ልጅ ንግሥት ሰብለ ወንጌል በ1680 ዓ.ም እና ባለቤቷ ደጃዝማች ዲሜጥሮስ በ1981 ዓ.ም በሞት ከተለዩ ጀምሮ አሁንም ድረስ አጽማቸው በሳጥን ሁኾ ይገኛል ነው ያሉት። ከገዳሟ በቅርብ ርቀት የሚገኘው ፍርስራሽ ቤተመንግሥትም ይገኛል ብለዋል።
በ1979 ዓ.ም እና በ1980 ዓ.ም ሳር የነበረው የጣራ ክዳን ወደ ቆርቆሮ፤ በ2004 ዓ.ም ደግሞ ሕንጻው የመሰንጠቅ እና የእቃ ቤቱ ምድር ቤት መወጣጫ የማርጀት ሁኔታ ገጥሞት ስለነበር በክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም በማኅበረሰቡ ተሳትፎ ጥገና እንደተደረገለት ጠቅሰዋል።
የስዕል ሥራዎቹ ደግሞ የጥንቱን የአሳሳል ጥበብ እንደጠበቀ በ2010 እና 2011 ዓ.ም የፌዴራል ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የገንዘብ እና የሙያ ድጋፍ በማድረግ እድሳት ተደርጎለታል ብለዋል።
ቅርሶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው እና ለተተኪ ትውልድ እንዲተላለፋም ሙዚየም ለመገንባት እንቅስቃሴ ላይ መኾናቸውን ገልጸውልናል። በጎ ለጋሾች እና የሚመለከታቸው አካላትም እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!