ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአረንጓዴ ጥቅጥቅ ደኑ ይታወቃል፡፡ ወጣ ገባ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ እና የብዝኀ እጽዋት ስብጥሩ ለዱር አራዊትም ምቹ ነው። በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦከምከም ወረዳ የሚገኘው የጣራ ገዳም፡፡
ስለ መስህብ ቦታው ለአሚኮ ማብራሪያ የሰጡት በሊቦ ከምከም ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ባለሙያ ተስፋሁን እያየ ይህ ስፍራ ከምድርም ከአየርም ላይ ጎልቶ ይታያል አሉ፡፡ 200 ሄክታር ስፋት እንዳለውም ይገመታል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ የሚገኘው ጣራ ገዳም የተፈጥሮ ጥብቅ ደን ከአዲስ ዘመን ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ ላይ ይገኛል።
ደኑ ከባሕር ዳር – ጎንደር የሚያስኬደው የአስፓልት መንገድ ግራ እና ቀኝ አቅፎ ይገኛል።
በዙሪያው የዋሻ እንድሪያስ እና የወይን ዋሻ ተክለሃይማኖት ገዳማት እንዲሁም ሌሎችም ተፈጥሯዊ እና መንፈሳዊ መስህቦችን አቅፎ እንደያዘ ተስፋሁን ጠቁመዋል።
የዋሻ እንድሪያስ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ አካባቢ በአጼ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት አቡነ እንድሪያስ የተባሉ መንፈሳዊ አባት ቶማስ ከተባለ እና ከሌሎች ተከታዮቻቸው ጋር ወደ ዋሻው በመምጣት ስፍራውን የክርስትና ሃይማኖት ማስተማሪያ እንዳደረጉት ይነገራል።
ዋሻ እንድሪያስ ውስጥ ለውስጥ 20 ኪሎ ሜትር ዋሻ እንዳለውም ነግረውናል። የውስጥ ለውስጥ መንገዱም ተክለሃይማኖት በተባሉ የሃይማኖት አባት ስም ከሚጠራው ወይን ዋሻ ጋር እንደሚያገናኝ እና ሁለቱ መንፈሳዊ አባቶችም በዋሻው ውስጥ ለውስጥ እስከ ዜና ማሪያም (አዲስ ዘመን ከተማ መውጫ) ድረስ እየተጓዙ ያስቀድሱ እንደነበር ይነገራል። የሁለቱ ዋሻዎች መገናኛ አጓት ማፍሰሻ በሚልም ይታወቃል ብለዋል።
በደን ተሸፍኖ ገደል ስር የሚገኘውን የዋሻ እንድሪያስ ቤተክርስቲያን ለሚጎበኝ ሰው የዋሻውን እና የቤተክርስቲያኑን ታሪኮች እና አሁናዊ ሀቆችን ያገኛል፡፡
በጣራ ገዳም ሥር የሚገኘው ሌላው ዋሻ ደግሞ ዙሪያውን በደን እና በገደል የተከበበው ወይን ዋሻ ተክለሃይማኖት ነው። የቤተክርስቲያኑ ሥራ በአጼ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት ተጀምሮ፤ በአጼ ሰይፈ አርዕድ (ከ1336 እስከ 1363 ዓ.ም) እንደተጠናቀቀ ታሪኩ እንደሚያስረዳ ባለሙያው ነግረውናል።
የጣራ ገዳም ደን በተለያዩ የተፈጥሮ ዛፎች የታደለ፣ የሀገር አቋራጭ አስፋልት መንገድ የሚያቋርጠው እና ነፋሻማ በመኾኑ ለመዝናኛነት ተመራጭ ነው፡፡ በሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚጋቡ ሙሽሮችም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱንም፣ መዝናናቱንም በአንድ ላይ ይከውኑበታል፡፡
ጣራ ገዳም ከሃይማኖታዊ ታሪኩ በተጨማሪ የተፈጥሮን ሚዛን ጠብቆ ንብን በማናባት ማር ለማምረት ያለው ጠቀሜታም ከፍተኛ ነው፡፡
ጣራ ገዳም ደን አሁንም በሕዝብ ተሳትፎ የሚጠበቅ እና ተከብሮ የሚገኝ የሀገር ሃብት ነው፡፡
ጣራ ገዳም ደንን እና በዙሪያው የሚገኙትን ሃይማኖታዊ እና ተፈጥሯዊ ቦታዎች መጎብኘት ከሃይማኖታዊ ፋይዳው በተጨማሪ መንፈሳዊ እርካታን ይሰጣል። የሀገርን ታሪክ ባሕል እና አሁናዊ ማንነት በማወቅ ለሌሎች ለማሳወቅ እና ለትውልድ ለማስተላለፍም ይረዳል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!