“የፈረንጅ መሳሪያ ቢመጣ አሸብርቆ የሀገር መገለጫ እንዴት ነሽ መሰንቆ”

0
27
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዝማሪዎች ልዩ ሥፍራ አላቸው። ሀገር ስትወረር በጥበባቸው ጀግኖችን ሰብስበዋል። ጦር ሜዳ ድረስ በመዝለቅ አበርትተዋል። ድል ይመጣ ዘንድም ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በኢትዮጵያ የነጻነት ታሪክ ውስጥ የእነርሱ ድርሻ ጉልህ ነው።
ጥበባቸውን ለሀገር ይጠቀሙበታል። በጥበባቸው ታሪክ አስተምረዋል። ባሕል ነግረዋል። ብርቱን አበርትተዋል። ሰነፍን ደግሞ ነቅፈዋል።
አዝማሪዎች የሚያሳዩት ክዋኔ የብዙዎችን ቀልብ ይስባል። የንጉሥን እና የንግሥትን፣ የመኳንንትን እና የመሳፍንትን፣ የጦር አበጋዞችን እና የሹማምንቱን ቀልብ ሲስብ ኖሯል። አሁንም መዋደዳቸው እና መሞገሳቸው ቀጥሏል። በዚህ ዘመን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብ የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ለጎብኝዎች የአካባቢውን ታሪክ እና ባሕል በክዋኔያቸው ያስተዋውቃሉ።
አዝማሪ እሱባለው አማረ ይባላሉ። እናቴም አባቴም አዝማሪዎች ነበሩ፤ እኔም ከእነርሱ ወርሼ አዝማሪ ኾኛለሁ ይላሉ። አዝማሪ ከጥንት ጀምሮ የመጣ ነው ብለዋል።
አዝማሪ ማለት አዘመረ፣ አመሠገነ ማለት እንደኾነም ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል። “ለኔ አዝማሪ ማለት መኩርያየ፣ ሰዎችን ማስደሰቻየ እና ማስተዋወቂያየ ነው” ይላሉ።
ቀደም ሲል የአዝማሪ ሥራ ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው ነበር የሚሉት አዝማሪ እሱባለው አማረ አሁን ላይ የአዝማሪዎች ሙያ እና የሚሠሩት ሥራ እየታወቀ እንደኾነም አስረድተዋል።
“ኧረ እናንተ ሰዎች ከታሪክ ተማሩ
ጥንት አባቶቻችን ምን እንደነበሩ፤
ዳዊት በበገና እያጫወታት
እዝራ በመሰንቆ እያጫወታት
ሳታየው አለፈች ያን መላከ ሞት» በማለት በመሰንቆ ያዜሙት አዝማሪው አዝማሪነት ማመስገኛ፤ መማዘጸኛም ነው ይላሉ።
በአዝማሪነት ሞያ ከ30 ዓመታት በላይ እንደሠሩም ተናግረዋል። ሙያውን የ14 ዓመት ልጅ ሳሉ እንደጀመሩትም ገልጸዋል።
አሁንም ድረስ በአዝማሪነት ሙያ መቀጠላቸውን ነው የገለጹት። በተለይም አሁን ላይ ዘርፉን ለማዘመን እንዲቻል አዝማሪ እሱባለው ከባልደረቦቻቸው ጋር የአዝማሪዎች ማኅበር በመመሥረት እየሠሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
“ማኅበራችን እንግዶች ከውጭ ሲመጡ ከአውሮፕላን ማረፍያ ጀምሮ አቀባበል ያደርጋል” ብለዋል።
አዝማሪ እና አዝማሪ ቤቶች ዘመናይነትን ሳይኾን የማኅበረሰቡን ትክክለኛ ባሕል እና ወግ አውጥተው ለጎብኝዎች በሚማርክ አቀራረብ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል ።
ሕዝቡ የራሱ የኾነነ ልዩ ምግብ እና መጠጥ ያለው፤ ልዩ የኾነ የአመጋገብ ሥርዓትን እና የአዘፋፈን ስልትን የሚከተል በመኾኑ አዝማሪ እና የአዝማሪ ቤቶች እነዚህን በግልጽ የሚያሳዩ መኾን አለባቸው ነው ያሉት። አሁን ላይ እየተሠራ ያለውም ይሄን ለማሳየት እንደኾነ ነው ያብራሩት።
እንግዳ ሲመጣ ውድ ውስኪ ገዝተን ማቅረብ ሳይኾን አጎዛ አንጥፈን፣ በሳር ቤታችን የባሕል ልብስ ተላብሰን፣ ጀንዴውን፣ አጎዛውን፣ ሰሌኑ ጥለን፤ በዋንጫ ጠላ፣ በብርሌ ጠጁ፣ በመለክያ አረቄው፣ በመሶብ እንጀራውን አቅርበን መኾን አለበት ነው የሚሉት። ቡናውም ቀራርቦ ያኔ አዝማሪው ጋቢውን አጣፍቶ፣ ጃኖውን ለብሶ ወዲህና ወዲያ ሲል ነው ባሕሉ የሚያምር ይላሉ። መገለጫ ባሕላችም ይህ ነው። ያንን ለማስተላለፍ ነው ትግል እያደረግን ያለነው ብለዋል።
በተናጠል ከሚሠራው ሥራ ይልቅ በጋራ በመኾን በአንድነት ባሕሉን ለማስተዋወቅ የአዝማሪ ቤቶች በሙሉ አቅም ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ እንዲፈጠርም አዝማሪ እሱባለው ጠይቀዋል። የጸጥታ ችግሩ የአዝማሪ ቤቶችን ሥራ ፈትኖት እንደቆየም ተናግረዋል።
አዝማሪ አስማማው ዳኝው አዝማሪዎች የሀገርን ባሕልና ታሪክ የሚናገሩ ናቸው ይላሉ።
“የፈረንጅ መሳሪያ ቢመጣ አሸብርቆ
የሀገር መገለጫ እንዴት ነሽ መሰንቆ” ይላሉ የመሰንቆን ሀገር መግለጫነት ሲናገሩ። አዝማሪዎች ለቱሪዝም ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው ብለዋል። መሰንቆም የሀገር ባሕል መግለጫ መሳሪያ እንደኾነ ነው የተናገሩት ።
ኢትዮጵያ ውስጥ አዝማሪ ብዙ ትኩረት ያልተሰጠው ግን ደግሞ ቢሠራበት ለአንድነት እና ለልማት ያለው አበርክቶ ከፍ ያለ ነው ብለዋል። የአዝማሪዎች ቤት ከተዘጋ ሙያው ብቻ ሳይኾን የሚጎዳው ባሕሉ፣ ጥበቡ እና የቱሪስት መስህብነቱም ነው ይላሉ።
ተተኪ ትውልድን ለማፍራትም ዘርፉን ማጠናከር እና ማልማት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሙዚቃ ጥበባት ባለሙያ ይታያል እንማው አዝማሪዎች እና የአዝማሪ ቤቶች ባሕልን ከማስተዋወቅ አንፃር ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
ይህን ጊዜ የማይሽረው ሥራቸውን ለትውልድ ማሽጋገር እንደሚባም ጠቁመዋል። እንደ ባሕል እና ቱሪዝም አዝማሪዎች እና የአዝማሪ ቤቶች የተሻሉ ሥራዎች እንዲሠሩ ለማስቻል የታቀዱ ሥልጠናዎች አሉ ነው ያሉት።
ብዙ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። አሁን ላይ ተፈጥሮ በነበረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት በጅምር የቀሩ ሃሳቦችን በማጠናከር የተሻለ እንዲኾኑ ለማድረግ የሚሠራበት ጊዜ መኾኑንም ጠቁመዋል። ቢሮው የተለያዩ የልምድ ልውውጦችን በማዘጋጀት ተበታትኖ ያለውን አዝማሪ የማሠባሠብ ሥራ እንደሚሠራም አብራርተዋል።
ሁሉንም ወደ አንድ ማዕቀፍ በማምጣት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በአንድ ላይ የሚሠሩበት ዕድል ይፈጠራል ነው ያሉት። ለዚህ ግን ሰላም እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት።
ሰላምን በሚገባ ማረጋገጥ ከተቻለም የባሕል ቤቶቹ የማይከፈቱበት ምክንያት እንደሌለም አስገንዝበዋል።
ባሕል እና ወግ የሚተዋወቁበት የተለያዩ መድረኮች ከምሽት በተጨማሪ ቀን ላይ የሚታዩበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ተናግረዋል። ታላላቅ ሆቴሎችም አዝማሪን አካትተው እንዲሠሩ እና ባሕል እና ወግን የሚመጡ ቱሪስቶች እንዲያውቁ ለማስቻል ሥራዎች እንደሚሠሩም አንስተዋል።
“ችግር አቦራ ነው ይራገፋል አሁን
እባክህ ፈጣሪ ሀገር ሰላም ትሁን” አዝማሪዎች ሀገር ሰላም ትኾን ዘንድ የተቀኟት ናት። አዝማሪ በችግር ጊዜ ለሀገር ሰላም ይጸልያል፤ በሰላም ጊዜ ደግሞ ደስታን ይጨምራል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here