ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጣና ሐይቅ የባሕር ዳር ውበት ነው። ይህ ሐይቅ በዘንባባዎቿ ለምትታወቀው ባሕር ዳር ልዩ ጌጧ ነው። ባሕር ዳርን ያለጣና ማሰብ ከቶ የማይቻልም ነው።
ይህ ውበት ታዲያ ለብዙ ዘመናት በጥሻ እና ዛፎች በመታፈን ከከተማው ተለያይቶ ቆይቷል።
አሁን የተጀመረው የጣና ዳር ልማት ጣና እና ባለዘንባባዋ ባሕርዳር ተመጋጋቢ ኾነው አንዱ የሌላው ውበት እንዲኾን እየተሠራም ይገኛል።
አሁን ላይ የጣና ዳር ልማት ጣናን ገለጥለጥ አድርጎታል። ይህ የልማት ሥራም በተለያዩ የጣና አቅጣጫዎች ባሕርዳር ከተማ እየሠራችው ከምትገኘው የኮሪደር ልማት ጋር በመተሳሰሩ አካባቢውን የውበት ምንጭ እንዲኾን አስችሎታል።
የጣና ዳር ልማት ለባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎችም የመንፈስ ማደሻ እና ከሥራ በኋላ ድካምን የማሳረፊያ አንድ አማራጭ ኾኖ ቀርቧል።
የጣና ዳር ልማቱ ጣናን ግልጥ አድርጎ ከመዝናኛነቱ ባሻገር ከተማዋን ነፋሻማ እና ውብ አየር እንድታገኝ በማድረግ በኩል አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ነው።
በጣና ሐይቅ ዳርቻ እየተገነባ የሚገኘው ፈለገ ግዮን ሪዞርት፣ በአማሩ ዘንባባዎች ግርጌ ተውበው የተሠሩ የኮሪደር ልማቶች እና የውስጥ ለውስጥ የእግረኞች መንገድ እና ሌሎችም ተያያዥ የሐይቁ ዳርቻ ልማቶች ባሕር ዳርን ድርብ ውበት አላብሰዋታል።
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ የዘንባባ ዛፎች የባሕር ዳር ከተማ ልዩ ምልክቶች ናቸው።
በአዲስ እየተገነቡ የሚገኙ የእግረኛ እና የብስክሌት መተላለፊያ መንገዶችም በዘንባባዎች ጥላ ሥር መራመድን የበለጠ ማራኪ አድርገውታል።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃ እና የቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ሙሉዓለም አያና የጣና መከፈት የባሕር ዳር ውበት ይበልጥ አፍክቶታል አሉ።
የልማት ሥራዎች መመጋገብ እና መተሳሰር ሲችሉ ውጤት እንደሚያመጡም የታየበት ሥራ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
ነባር ዕሴቶች ላይ አዳዲስ ዕሴትን በመጨመር እና ለቱሪስቶች የሚመጥኑ ሆቴሎችን እና ሪዞርቶችን በመገንባት ከጣና ዳር ልማቱ ጋር የማያያዝ ሥራ እየተከናወነ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ጣናን ለቱሪስት ምቹ ከማድረግ አኳያ በሰፊው እየተሠራ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት።
ባሕር ዳር ለነዋሪወቿ ምቹ፣ ለቱሪስቶችም ሳቢ እየኾነች ነው ብለዋል ቡድን መሪው። የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስበውን ጣና ሐይቅ እና በውስጡ የሚገኙ ደሴቶችን የቱሪዝም ጸጋ በአግባቡ ለይቶ በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማላቅ ይገባልም ብለዋል።
ባሕር ዳር ከተማ ከሌሎች ከተሞች ጋር ያላትን የቱሪዝም ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከተማዋ ቀጣይነት ያለው እና ከዚህም በላይ የጎላ ውበት እንዲኖራት የጣና ዳር ልማቶችን በሰፊው የማልማት፣ ቱሪዝምን የማነቃቃት፣ የጎብኝዎችን ቆይታ የማራዘም እና መሰል ሥራዎች ታቅደው እየተከናወኑ ነው፤ ለውጥም እየታየባቸው ነው ብለዋል።
የጣና ዳር ልማቶች በፍጥነት እና በጥራት እየተከናወኑ ስለመኾኑም ነው የገለጹት። ይህንን ተፈጥሯዊ ውብ አካባቢ በአግባቡ የማልማቱ ሂደት የቱሪዝሙን ዘርፍ ከማነቃቃት ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርም ማገዙን ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ ተጠናቅቀው ለሕዝብ ክፍት በኾኑት እንደ ጣና ፓርክ አይነት መናፈሻዎች ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው እየተዝናኑበት ነው።
ሙሽሮች ሰርጋቸውን በዚያው እያካሄዱ፣ ቤተሰቦች ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር በመኾን እየተዝናኑበትም ነው ብለዋል።
ይህ ሰው ተኮር የልማት ሥራ የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን በመሳብ ከሚያስገኘው የገጽታ ግንባታ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ ለነዋሪዎችም የመዝናኛ እና የማንበቢያ አማራጭ ኾኗል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን