‎ከነ ትናንትናዋ በትናንትናዋ ስፍራ ያለች ታሪካዊቷ ደብረሲና ማርያም

0
24
ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚገኘው ምዕራብ ደንቢያ ወረዳ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ቅርሶች በስፋት የሚገኙበት ወረዳ ነው፡፡
‎የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ሳቢ ተፈጥሮ እና አይነ ግቡ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ፣ የጣና ሐይቅ ዳርቻ፣ ምቹ የአየር ጸባይ፣ ለም አፈር እና እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ያለበት አካባቢ ነው።
‎በወረዳው ከሚገኙ የመስህብ ሃብቶች መካከል በጎርጎራ ከተማ የምትገኘው ምዕራፈ ቅዱሳን ደብረሲና ጽዮን ማርያም አንድነት ገዳም ተጠቃሽ ናት።
‎ዕድሜ ጠገቧ፣ የታሪክ ማኅደር የኾነችው ጥንታዊቷ እና ታሪካዊቷ ምዕራፈ ቅዱሳን ደብረሲና ጽዮን ማርያም አንድነት ገዳም በጣና ሐይቅ ዳርቻ በጎርጎራ ከተማ ትገኛለች።
‎ ከጎንደር በ64 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ደብረ ሲና በዙሪያዋ አብረዋት ዓመታትን የኖሩ ዕድሜ ጠገብ ረጃጅም ዛፎች፣ የጣና ሐይቅ እና በቅርቡ የተገነባው ዘመናዊው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ይገኛሉ።
‎ውበትን ከታሪክ የተጎናጸፈችው ደብረሲና ማርያም እጅግ ውብ እና ጸጥታ የተሞላበት ስፍራ ላይ የምትገኝ በእንጨት፣ በድንጋይ እና በጭቃ የተሠራች ጥንታዊት ገዳም ናት፡፡
‎የገዳሟ አሥተዳዳሪ አባ ገብረ ማርያም ኪዳነ ማርያም ገዳሟ በ1312 ዓ.ም በአጼ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት እንደተመሠረተች ይናገራሉ፡፡ ዘመንን መሠረት ያደረገ የአሠራር ለውጥ ወይም እድሳት አላደረገችም ነው ያሉት፡፡
ይልቁንም የትናንት አባቶችን ታሪክ ይዛ በመቆየት አሁን ላለው ትውልድ ያስረከበች እና ለነገው ሀገር ተረካቢም ይዛ የምትቆይ ናት ብለዋል፡፡ ቤተክርስቲያኗ እስካሁን ድረስ በሣር ክዳን ላይ እንደኾነችም ገልጸውልናል። ከሳር ክዳኗ ውጭ በየጊዜው የሚታደስ ነገር የላትም ነው ያሉት።
‎የቤተክርስቲያኗ የውስጠኛው ክፍል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥዕሎች የተመላ ነው። የግድግዳ ሥዕሎቹን እቴጌ መለኮታዊት እንዳሳሏቸው ተናግረዋል።
ሥዕሎቹ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት እድሳት ያልደረገላቸው እና የቆየውን የቤተክርስቲያን አሣሣል ዘይቤ የሚያሳዩ እንደኾኑም ገልጸዋል፡፡ ‎የግድግዳ ላይ ሥዕሎቹ የዘጠኙ ቅዱሳንን ታሪክ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ከውልደት እስከ ዕርገት፣ የድንግል ማርያምን ታሪክ፣ የሰማዕታት እና የቅዱሳንን ታሪክ የሚያስረዱ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
‎በገዳሙ በርካታ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ይገኛሉ።የብራና መጻሕፍት፣ መስቀሎች፣ የነገሥታት ዘውዶች፣ እና ሌሎች ቅርሶችም ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ቅርሶች በሙዚዬም ተዳራጅተው ለጉብኝት ክፍት መኾናቸውንም ገልጸውልናል፡፡
‎የገዳሟ ስምንት ከእንጨት የተሠሩ በሮች እና ስምንት መስኮቶች፣ 29 ምሰሶዎች ሳያረጁ እና ሳይታደሱ ዛሬም ድረስ አሉ። ደብረሲና ማርያም ቱሪስቶችን የምትስብበት ዘመን በተሻገረ ጥበብ የተሞላበት የውስጥ የግድግዳ ላይ ሥዕሎቿ ናቸውም ብለውናል።
እነዚህ ሥዕሎች የበርካታ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችን ቀልብ እንደሳቡ ዛሬም ድረስ አሉ ይላሉ፡፡ ከ350 ዓመታት በላይ ያለ እድሳት የኖሩ ስዕሎቿ ትናንትናን ያሳያሉ ነው ያሉት፡፡
‎በዚች ገዳም ውስጥ የምትገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ከግብጽ እንደመጣችም ይነገራል። ሥዕሏን ለየት የሚያደርጋት እቴጌ መለኮታዊት በልዩ ሱባዔ በእንባ እንዳሠሯት እና ወደ ግብጽ በሥርቆት ተወስዳ በተአምር እንደተመለሰች ይነገራል ነው ያሉት።
ለዚህም ምዕመናን ይህችን ሥዕል ግብጻዊት ማርያም እያሉ ይጠሯታል ብለዋል። በታሪክ ምዕራፍ ተጠብቃ መዝለቋ ክብሯን ከፍ አድርጎታል ይላሉ አባ ገብረ ማርያም፡፡ ደብረሲና ማርያም ከነትናንትናዋ በትናንትናዋ ስፍራ ያለች ናት።
‎በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ የባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የመዳረሻ ልማት ባለሙያ ዲያቆን ጥጋቡ አጃው ደብረሲና ማርያም ቤተ ክርስቲያኗ ጥንታዊነቷን የጠበቀች እና በውስጧም በርካታ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ያሏት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች የሚጎበኟት ናት ብለዋል።
‎በየዓመቱ ኅዳር 21 ዓመታዊ የንግሥ በዓል የሚከበርባት እንደኾነችም ገልጸዋል። ለዘንድሮው ክብረ በዓልም በደመቀ ሁኔታ ለማክበር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
‎የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ጌታሰው ታደለ በገዳሟ የሚገኙ ቅርሶችን ለመጠበቅ በቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ላይ የጽዳት እና የእንክብካቤ ሥራዎች እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
‎በገዳሟ የነበረውን የምስጥ ስጋት ለማስወገድ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ከባሕል እና ቱሪዝም ጋር በመተባበር የቅርስ ይዘቱ እንደተጠበቀ በ2016 ዓ.ም የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትን በገነባው ቢአይካ ተቋራጭ ድርጅት በተገኘ ድጋፍ ወለሉ የኖራ ጥገና ተደርጎላታል ብለዋል።
ወደ ገዳሟ የሚወስድ የአስፋልት መንገድ መሠራቱንም አንስተዋል። የመስህብ ሃብቱን የሚያስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here