“የአንድነት ማዕድ መቁረሻ፤ የፍቅር መናገሻ”

0
261

ባሕር ዳር: የካቲት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ታናሽ እና ታላቅ ሳይለዩበት፣ ደሃ እና ሀብታም ሳይባልበት፣ አፈር ገፊ ሳይባልበት መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ንጉሡ እና ንግሥቲቱ ሁሉም በአንድነት ይገናኙበታል። በአንድነት በአንድ ጣራ ሥር ይሰባሰቡበታል፤ በፍቅር ይነግሡበታል፤ በደስታ ማዕድ ይቆርሱበታል፤ ከጠጁ ይጎነጩበታል፤ ከጮማው ይቆርጡበታል፡፡

አንድ ጣሪያ ለሁለት ወንዞች የሚገብሩበት፣ ንጉሡ ከሚወዳቸው እና ከሚወዱት ሕዝብ ጋር የሚገናኙበት፣ ሰው ሳይመርጡ የሚጠሩበት፣ ከለጋስነታቸው ሳያጎድሉ ግብር የሚያበሉበት፣ ከደግነታቸው ሳያሳንሱ የሚሰጡበት፣ ከግብር ማብላት ባሻገር የሕዝባቸውን ልብ የሚመረምሩበት፣ መደሰቱን እና መከፋቱን የሚያውቁበት፣ ታሪክ የተሠራበት፣ ታሪክ የሚነገርበት፣ የጥበበኞች ጥበብ ያረፈበት ውብ ሥራ፡፡

በዚያ ያማረ የግብር አዳራሽ ውስጥ ንጉሡ ከሕዝባቸው ጋር ማዕድ ይቆርሳሉ፤ ከሕዝባቸው ጋር ደስታን ይጋራሉ፡፡ ያም ያማረ አዳራሽ አይጠየፍ ነው፡፡ አይጠየፍ ሁሉን የሚሠበሥብ፣ ሁሉንም አንድ የሚያደርግ፣ ሁሉንም በአንድ ጣሪያ ውስጥ የሚያገናኝ የተዋበ ነው፡፡

ወሎ ተንታ የተወለዱት፣ ከደጋጎቹ እና ከጀግኖቹ ወገን የኾኑት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አሻራቸውን ያሳረፉት፣ ኢትዮጵያን እደፍራለሁ፣ ሕዝቦቿን አስገብራለሁ፣ ሃብትና ንብረቷን እወስዳለሁ፣ የቀደመ ማንነቷን፣ የኖረ እና የሚኖር ነጻነቷን፣ ጥርጣሬ የሌለበት ተስፋዋን እነጥቃለሁ ብሎ በተነሳ ጠላት ላይ የዘመቱት፣ በታላላቅ ጦርነቶች ዘምተው፣ ተዋግተው አዋግተው ሀገር ያስከበሩት ንጉሥ ሚካኤል የግብር አዳራሻቸው ከባሕሪያቸው ጋር ይመሳሰላል ይሏቸዋል፡፡ ለምን ቢሉ እሳቸው ሰው ወዳጅ፣ ሁሉንም በእኩል ዓይን የሚያዩ ታላቁን አክብረው ታናሹን የማይንቁ የማይጠየፉ ናቸውና አዳራሹም ሳይጠየፍ ሁሉንም ያስተናግዳልና፡፡

ንጉሥ ሚካኤል ቻይ እና አስታዋይ መኾናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ቻይነታቸውም በነገሥታቱ ዘንድም የታወቀ እና የተመሰከረ ነበር፡፡ ለአብነት ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ በንጉሥ ሚካኤል እና በራስ ወሌ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ችግር እንዲበርድ ደብዳቤ በላኩላቸው ወቅት “ አንተ ወትሮም ቻይ ነህና እንደቀድሞው ቻለው” ብለው መጻፋቸውን ዶክተር ምሥጋናው ታደሰ ሚካኤል ንጉሠ ወሎ ወትግሬ በተሰኘው የታሪክ መጻሕፋቸው አስፍረዋል፡፡

ንጉሡ በዘመናቸው አሳርፈዋቸው ካለፉት አሻራዎች መካከል አይጠየፍ የግብር አዳራሽ አንደኛው ነው፡፡ ንጉሥ ሚካኤል ከተንታ ጀምሮ እንደ አባቶቻቸው ሁሉ ግብር ማስገባት እና ግብር ማብላት የተለመደ ተግባራቸው ነበር፡፡ ግብሩንም የሚያበሉት በድንኳን ነበር፡፡ በኋላ ግን ከራስነት ወደ ንጉሥነት ከፍ ብለው፤ ከተንታ ወደ ደሴ መጥተው፣ ግዛታቸውም በሰፋ ጊዜ የግብር አዳራሽ ይኖራቸው ዘንድ ወደዱ፡፡

ምሥጋናው ታደሰ (ዶ.ር) በታሪክ መጻሕፋቸው “ከራስነት ወደ ንጉሥነት ማደጋቸውን ተከትሎ የሠራዊታቸው፣ የመሳፍንቶቻቸው እና በአጠቃላይ የአገልጋዮቻቸው ቁጥር በመጨመሩ እንደቀድሞው በድንኳኖች ውስጥ ግብር ማብላት ለአሠራር አስቸጋሪ ኾኖ ተገኝቷል፡፡ በመኾኑም ሁኔታው ንጉሥ ሚካኤልን ሰፊ የግብር አዳራሽ እንዲሠሩ አስገድዶአቸዋል” ብለው ጽፈዋል፡፡

ግብር ማብላት በኢትዮጵያ ነገሥታት ዘንድ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ በሕዝቡ፣ በመሳፍንቱ፣ በነገሥታቱም ዘንድ ጥሩ ግንኙነት እንዲፈጠር ያደርጋል ይባላል፡፡
በንጉሥ ሚካኤል ቤተ መንግሥት አስጎብኚዋ ተስፋ ማርያም ባረኩ ንጉሥ ሚካኤል በደሴ የሚገኘውን ቤተ መንግሥታቸውን አሠርተው ከመምጣታቸው አስቀድሞ በትውልድ ቀያቸው በተንታ ወረሂመኑ ኾነው ወሎን ያሥተዳድሩ ነበር። በዚያም በድንኳን ግብር ማብላት የተለመደ ተግባራቸው ነበር ይላሉ፡፡

አስጎብኚዋ እንደነገሩን አይጠየፍ አዳራሽ በንጉሥ ሚካኤል ቤተ መንግሥት ቅጥር ውስጥ ሲገቡ በመጀመሪያ የሚገኝ ነገር ግን በመጨረሻ የተሠራ ሕንጻ ነው፡፡

ታላቁ የግብር አዳራሽ 1907 ዓ.ም ገደማ እንደተሠራ ይነገራል፡፡ ምሥጋናው ታደሰ (ዶ.ር) ስለ አይጠየፍ ሲጽፉ “ የአዳራሹ ግንባታ በ1906 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ተጀመረ፡፡ አዳራሹ የተሠራበት ዘመን በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ የገቡበት እና በሀገራችን የግንባታ ዘርፍ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የተሰማሩበት ጊዜ ስለነበር ንጉሥ ሚካኤልም ይህንን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመውበታል፡፡ አዳራሹ የተሠራበት እንጨት ከደሴ ከተማ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ከሚገኘው እና በደን ሀብቱ ይታወቅ ከነበረው ከአልብኮ ወረዳ ሳልመኔ አካባቢ ነው የተጓጓዘው፡፡ ከእንጨቱ ግዝፈት የተነሳ አንዱን ግንድ ከ60 እስከ 70 ሰዎች ነበር የሚሸከሙት፡፡ የመንገዱ ሁኔታ የተመቸ ባለመኾኑ እንጨቱን ከሚያጓጉዙት ሰዎች በርካታዎች ይቆስሉ አንዳንዶቹም ለሞት ይዳረጉ ነበር፡፡

አሸዋ እና ድንጋይ በቅርብ ከሚገኙት የቦርከና እና የገራዶ ወንዞች ኖራ ደግሞ አምባሰል ውስጥ ሰጎራ ከተባለ ቦታ ነበር የተሠበሠበው፡፡ ኖራው ከስንዴ ዱቄት እና ከእንቁላል ጋር ተቀላቅሎ እንደ ሲሚንቶ እንዳገለገለ ይነገራል፡፡ 2 ሺህ 131 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው እና 45 ሜትር በ27 ሜትር ስፋት ያለው ይህ የግብር አዳራሽ አስር ሜትር ቁመትና 1 ሜትር ውፈረት ባላቸው ሰባ ምሰሶዎች የተዋቀረ ነው፡፡

አዳራሹ የብዙ ጥበበኞች ዕውቀትና ጉልበት የፈሰሰበት ውበትን የተጎናጸፈ አዳራሽ ከዘጠኝ ወራት ግንባታ በኋላ በ1907 ዓ.ም ተጠናቀቀ” ብለው ጽፈዋል ዶክተር ምሥጋናው፡፡ የግብር አዳራሹ የተጠናቀቀው በወራት ልዩነት ነው፡፡ ንጉሥ ሚካኤል ኪነ ሕንጻዎችን በቀናት እና በወራት ውስጥ ማጠናቀቅ መለያቸው ነው፡፡
አስጎብኝዋ ደግሞ ከውጭ 70 ከውስጥ 20 መሰሶዎች ያቆሙት የግብር አዳራሽ እንደኾነ ነግረውናል፡፡

ታላቁ የንጉሥ ሚካኤል የግብር አዳራሽ አይጠየፍ ተሰኘ፡፡ አይጠየፍ ማለት ዘር፣ ብሔር፣ ቀለም ሳይለይና የመደብ ልዩነት ሳይደረግ ጌታ ከአሽከሩ እመቤት ከአገልጋይዋ ጋር በአንድነት የሚስተናገዱበት ማለት ነው ብለው የታሪክ ጸሐፊው ዶክተር ምሥጋናው ጽፈዋል፡፡

ወደ አይጠየፍ የሚገቡት መሳፍንት፣ ካህናት፣ የእልፍ አስከልካዮች፣ የጦር አበጋዞች ብቻ አልነበሩም፡፡ ሁሉም አድልዎ ሳይደረግባቸው ይገቡ ነበር እንጂ፡፡ “አይጠየፍ የአዳራሹ ስም ብቻ አይደለም የሚካኤል ባሕሪም ጭምር እንጂ፡፡ አዳራሹ ያስገቡበትን የሚይዝ ግዑዝ ነገር ነው፡፡ ከተርታው ሕዝብ እንዲሁም ከድሆች ጋር በአንድ አዳራሽ መብላትን ከመናቅ ያልቆጠረው ንጉሥ እርሱ ነው አይጠየፍ” ብለው ጽፈዋል ምሥጋናው ታደሰ(ዶ.ር)፡፡ ሰውን መውደድ እና ሁሉንም በአንድነት መያዝ የወሎዬ ባሕሪም ነው፡፡

አስጎብኚዋ እንደነገሩኝ በግብር ማብላት ውስጥ ንጉሥ ግብሩ በሚገባበት ጊዜ አዝማሪዎች የሚገጥሙትን ግጥም እያዳመጡ የሕዝቡን የልብ ትርታ የሚሰሙበት፣ በቅኔ የተነገረውን የሚለዩበት ጊዜ ነበር፡፡

የሀገሬው ሰው ሥርዓት አክባሪ ነውና ወደ አዳራሹ ሲገባ ሥርዓት ጠብቆ፣ ሳይጋፋ በየተራ ነበርና
“ አዳራሹ ሰፊ በሩ አልጠበባችሁ
በተራ ተራ ምነው መግባታችሁ” ተብሎ ተገጥሟልም ብለውናል አስጎብኚዋ፡፡ በእርግጥ ከዚህ ያለፈ ቅኔ ማዘሉንም ነግረውናል፡፡ በዚህ የግብር አዳራሽ ለመግቢያ እና ለመውጫ የተዘጋጁ በሮች አሉ፡፡ ንጉሡም ኾነ ሕዝቡ ለመግቢያ የተጠቀሙበትን በር ለመውጫ አይጠቀሙበትም ይባላል፡፡

ንጉሥ ሚካኤል በአይጠየፍ የግብር ማብያ ውስጥ ዘር፣ ሃይማኖት፣ የሥልጣን እና የሃብት ደረጃ አለመለየታቸው ብቻ አልነበረም፤ ከግብሩ ባሻገር በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ሕግና ሥርዓትን በጥበብ ያስምሩበት፣ ከሚመሩት ሕዝብ ጋር ልብ ለልብ ይገናኙበት ነበር፡፡

አይጠየፍ በአንድ ጣሪያ ላይ ለሁለት ወንዞች ይገብራል ይሉታል፡፡ ምሥጋናው ታደሰ (ዶ.ር) “ ከአይጠየፍ አዳራሽ ጣራ የሚወርደው ፍሳሽ ለሁለት የሀገራችን ወንዞች ይገብራል፡፡ በሰሜን እና በምሥራቃዊ የጣራው ክፍል የሚወርደው ዝናብ ወደ ቦርከና ወንዝ ፈስሶ ለአዋሽ ወንዝ ሲገብር ከደቡብ እና ምዕራባዊ የጣራው ክፍል የሚወርደው የዝናብ ውኃ ገራዶ ወንዝ በመፍሰስ ለታላቁ የዓባይ ወንዝ ይገብራል” ብለው ከትበዋል፡፡ ይሄን እውነት አስጎብኚዋ ተስፋ ማርያምም ነግረውናል፡፡

የታሪክ ጸሐፊው እንደሚሉት ከግዝፈቱ፣ ከስፋቱ፣ ከአሠራር ጥበቡ ፣ ከእድሜ ጠገብነቱ አይጠየፍ የደሴ ከተማዋ ዋናው ታሪካዊ ቅርስ ነው፡፡ ዋናው የቱሪስት መስህብ ነው፡፡ ከከተማዋ የተለያዩ አቅጣጫዎች ከፍ ብሎ የሚታይ የደሴ ሠንደቅ እና ሞገስም ጭምር ነው፡፡ አይጠየፍ የደረሰ ሁሉ ታሪክ ይመራል፤ ትናንትን እና ዛሬንም ያመዛዝናል፡፡

ሀገር በአንድነት ትጸናለች፤ በፍቅር ትዋባለች፤ አይጠየፍ ብራና ነው አንድነት የሚገለጥበት፣ ፍቅር የሚማሩበት፡፡ አይጠየፍ የእኩልነት ማሳያ ነው ወገን የማይለይበት፤ ታናሽ እና ታላቅ የማይባልበት፤ ዘርና ቀለም የማይመረጥበት፡፡ ንጉሡ አስቀድመው ገና ትውልድ ሁሉ አንድነትን፣ እኩልነትን፣ ፍቅርን ሰላምን እና ተስፋ ገንዘቡ ያደርግ ዘንድ ሰውን ሁሉ አልጠየፍም ብለው አሳዩ፡፡ እርሳቸው ባለፉ ጊዜ ለታሪክ ምልክት ይኾን ዘንድም የማይጠየፍ የግብር አዳራሽ ሠርተው አለፉ፡፡

አበው ኢትዮጵያን ያጸኗት በአንድነት፣ በእኩልነት ተነስተው ነበር፡፡ በጠላቶቿ ፊት ያስከበራት፤ በነጻነቷ ያኖሯት፤ በክብር እና በሞገስ ከፍ ከፍ ያደረጓት በፍቅር ነው፡፡ አበው ጥለውት ያለፉት የማይታጠፍ አንድነትን፣ የማይናወጽ ጽናትን፣ የማይጠወልግ ኢትዮጵያዊነትን እንጂ ጥልና ጥላቻን አይደለም፡፡ መለያዬት ሀገር ታሳጣለች፣ መለያየት ደም ታፋስሳለች፣ አጥንት ታስከሰክሳለች፣ ሕይዎትም ትቀጥፋለች፡፡ የሀገር ፍቅር ማጣት ሁሉን ታሳጣለች፡፡ እንደ ንጉሡ ሁሉ ሰውን በእኩልነት ማዬት፣ በአንድነት መገናኘት፣ በጽናት መቆም፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን ማስቀደም የከበረች ሀገር እንድትኖር ያደርጋል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here