“በአማራ ክልል በመጀመሪያ ሩብ ዓመት የቱሪዝም መነቃቃት ተስተውሏል” አየለ አናውጤ (ዶ.ር)

0
40

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የተለያዩ ባሕሎችን፣ ቅርሶችን እና ታሪኮችን በጉያው አቅፎ የያዘ ባለጸጋ ነው።

በቀጣይ ወራት ደግሞ በአማራ ክልል በርካታ በዓላት የሚከበሩት፣ በርካታ ጎብኝዎች ወደ ክልሉ የሚገቡበት ነው። የልደት እና የጥምቀት በዓላት ደግሞ በርካታ ጎብኝዎችን የሚስቡ በዓላት ናቸው። በሚከበሩበት ሃይማኖታዊ በዓላትም ከመላው ኢትዮጵያ የሃይማኖቱ ተከታዮች ወደ አማራ ክልል ይመጣሉ።

እንግዳ ተቀባዩ የአማራ ክልል ሕዝብም እንግዶችን ለመቀበል ሽር ጉድ የሚልበትም ወቅት ነው።

ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) በጸጥታ ችግሩ ፈተና ላይ የነበረው የቱሪዝም ዘርፉ በማገገም ላይ ይገኛል ብለዋል።

በሩብ ዓመቱ ከፍተኛ የቱሪዝም መነቃቃት ተስተውሏል ያሉት ምክትል ኀላፊው የሀገር ውስጡም ኾነ የውጭ ጎብኝዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ነው ያሉት።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ ከ5 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ክልሉን መጎብኘታቸው ምሳሌ የሚኾን ነው ብለዋል። ከመጭው የልደት በዓል ጀምሮ ደግሞ ጥምቀት እና ሌሎች በዓላት ተጠባቂ ስለኾኑ ከዚህም በላይ ውጤት እንደሚመዘገብ እንጠብቃለን ነው ያሉት።

ለዚህም በሁሉም የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ እንደኾነ ነው የገለጹት። አገልግሎት ሰጭ ተቋማትንም እያወያዩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ላይ መሠረተ ልማት የማሟላት እና ምቹ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ እንደኾነም ገልጸዋል።

በዓላቱ በሰኬት እንዲጠናቀቁ እና ቱሪዝሙ እንዲነቃቃ ከወረዳ እስከ ክልል ላሉ የሥራ ኀላፊዎች እና ለሚመለከታቸው አካላት ቱሪዝምን የተመለከተ ሥልጠና መሠጠቱንም ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት የቱሪዝምን ጉዳይ ለተቋሙ ብቻ የመስጠት ነገር ነበር ያሉት ምክትል ኀላፊው በዚህ ዓመት ይህ አካሄድ አይሠራም ብለዋል። ቱሪዝም የዚህ ዘመን ቀዳሚ አቅጣጫ እንደኾነም ተናግረዋል።

ለቱሪዝሙ ዘርፍ መሳለጥ ሁሉም ያገባዋል ነው ያሉት። ይህን ግምት ውስጥ በማስገባትም የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ ጠንካራ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ከምንም በላይ በቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚው ማኅበረሰቡ በመኾኑ ሕዝቡ ለቱሪዝም ዘርፉ ባለቤት መኾን እንዳለበትም አሳስበዋል። ዘርፉ ሲነቃቃ ሁሉም ተጠቃሚ እንደሚኾን ተናግረዋል።

ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ታድያ ሰላም መሠረታዊ ነው ብለዋል። “ሰላም የቱሪዝም ፓስፖርት ነው” ያሉት ምክትል ኀላፊው እየተሻሻለ የመጣውን የሰላም ሁኔታ የበለጠ ማጠናከር እና ዘላቂ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ለዘላቂ ሁለንተናዊ ሰላም ሕዝቡ ባለቤት እንዲኾንም ጥሪ አቅርበዋል።

በእንግዳ ተቀባይነት ዘመን አይሽሬ ባሕል የሚታወቀው የክልሉ ሕዝብ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here