ባሕር ዳር፡ የካቲት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብት እና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የስድስት ወራት የሥራ እንቅስቃሴን ገምግሟል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ የተከናወኑ ተግባራትን ለቋሚ ኮሚቴ አባላት አቅርበዋል። የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ መስህቦች ባለቤት መኾኑን አንስተዋል። ዘርፉ ባለፉት ዓመታት የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ምጣኔ ሃብት በማሳደግ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረውም አንስተዋል።
በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ቦታዎችን በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ታቅዶ ወደ ሥራ ቢገባም በክልሉ በተከሰተው የሰላም እጦት የተፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ አጋማሽ በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ቦታዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ ከታቀደው ከ15 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች የጎበኙት ከ4 ሚሊዮን እንደማይበልጥ ገልጸዋል። ይጎበኛሉ ተብሎ ከታቀደው ከ27 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ውስጥ ማሳካት የተቻለው 10 ሺህ 400 እንደኾነ ተነስቷል።
በዚህም በግማሽ ዓመቱ ይሠበሠባል ተብሎ ከታቀደው ከ5 ቢሊዮን በላይ ብር ውስጥ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብቻ ማሳካት መቻሉን ነው ምክትል ኀላፊው የገለጹት። በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት የጎብኝዎችን እንቅስቃሴ ከመግታት ባለፈ ቅርሶችን ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ እንደ ችግር ተነስቷል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብት እና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ አበራሽ ታደሰ በክልሉ በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም የተለያዩ ክብረ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ በመደረጉ ዘርፉ መጠነኛ መነቃቃት ማሳየቱን ገልጸዋል።
በውጭ በሕንድ በሚገኙ ከተሞች እና በሀገር ውስጥ በጅግጅጋ ከተማ የክልሉን ባሕል የማስተዋወቅ ሥራ መሠራቱን በጥንካሬ አንስተዋል። ይሁን እንጅ በሰላሙ ችግር ምክንያት የጎብኝዎች እንቅስቃሴ መቀነሱን እና ቅርሶችን ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ ማነቆ መኾኑን እንደ ችግር አንስተዋል። የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ተቀናጅተው መሠረተ ልማት ማሟላት እንደሚገባም መክረዋል። የተዳከመውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ማኅበረሰቡ የሰላሙ ባለቤት እንዲኾንም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!