አዲስ አበባ: ጥር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር “የባሕል ጥበባት እና ስፖርት እመርታ ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት የመሥሪያ ቤቱን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።
በኢትዮጵያ የሚገኙ ልዩ ልዩ ባሕላዊ እሴቶችን፣ ቋንቋዎችን እና ሀገር በቀል እውቀቶችን እንዲኹም የስፖርት ዘርፉ እንዲጠኑ፣ እንዲጠበቁ፣ እንዲለሙ እና ለትውልድ እንዲሻገሩ በማድረግ በኩል በርካታ ተግባራት መከናወናቸው በዕለቱ ተነስቷል።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ ባለፉት ስድስት ወራት በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በተከናወኑ ሥራዎች በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሀገርን ባሕል ታሪክ እና ማንነት ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በስፖርቱ ዘርፍ የስፖርት ፖሊሲዎችን በማሻሻል በዘርፉም ውጤት እንዲመዘገብ በማድረግ በኩል በተለይም ከ22 ዓመት በኋላ ከ17 ዓመት በታች ታዳጊ ወጣቶች በእግር ኳሱ ውጤት እንዲያመጡ ተደርጓል ነው ያሉት።
በአትሌቲክስ ዘርፋም 49 ወርቅ 27 ብር 38 ነሐስ በድምሩ 89 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ተችሏል ብለዋል ።
የስፖርት ማዘውተሪያን በማስፋፋት ረገድም 43 ሺህ 335 የይዞታ ማረጋገጫ መሰጠቱን የጠቆሙት ሚኒስትሯ በበጀት ዓመቱ 1 ሺህ 560 የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችም እንደተገነቡ ተናግረዋል።
መንግሥት የስፖርት ልማት እድገትን ለማሳለጥ በታዳጊ እና ተተኪ ልማት ላይ በርካታ ሥራ እየሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ የስፖርት ልማቱ የበለጠ ውጤታማ እንዲኾን ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።
በኪነ ጥበብ ዘርፉ በተሠራው ሥራም የሀገርን መልካም ገጽታ በመገንባት ዘላቂ የኾነ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እና የሚቆጠሩ እና የሚጨበጡ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ነው የገለጹት።
ባለፉት ስድስት ወራት የሕዝብ እና የአደባባይ በዓላትን በመጠቀም ቱባ ባሕልን በማስተዋወቅ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን እና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









