ባሕር ዳር: የካቲት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና የሰሜኑ ጦርነት የቱሪዝሙን ዘርፍ ክፉኛ ከጎዱት ምክንያቶች ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ምጣኔ ሃብታቸው በቱሪዝሙ ዘርፉ ላይ የተመሠረቱ እንደ ላሊበላ ዓይነት ከተሞች ይበልጥ ተጎጅ ኾነዋል፡፡
የከተማ አሥተዳደሩ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ እንዳሉት ኮቪድ 19 ከመከሰቱ እና የሰሜኑ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በዓመት ከ40 ሺህ ያላነሰ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ከተማዋን ይጎበኙ ነበር፡፡
በ2014 ዓ.ም ደግሞ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ቁጥር ወደ 776 ወርዷል፡፡ በ2015 ዓ.ም በክልሉ በነበረው አንጻራዊ ሰላም ከ4 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች አካባቢውን ጎብኝተዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ በተከሰተው ግጭት በስድስት ወራት አካባቢውን የጎበኙት የውጭ ሀገር ጎብኝዎች 1 ሺህ 500 ብቻ ናቸው፡፡ ጎብኝዎቹ በብዛት በገና በዓል መታደማቸውንም ነው ያነሱት፡፡
አንድ የውጭ ሀገር ጎብኝ በሦስት ቀን 6 ሺህ 568 ብር ወጭ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት በስድስት ወሩ ከውጭ ሀገር ጎብኝዎች የተገኘው ገቢ 9 ሚሊዮን 852 ሺህ ብር ብቻ ነው፡፡
የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችም ባለፉት ዓመታት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ እንደኾነ ኀላፊው ገልጸዋል፡፡ የቱሪዝም እንቅስቃሴው በተለይም ደግሞ ከልደት በዓል ዋዜማ እስከ ጥር መጨረሻ በነበሩት ቀናት የተሻለ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት በቱሪዝሙ ዘርፍ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ የተሰማሩ ተቋማት እና ግለሰቦች ተጎጅ ኾነዋል፡፡ በሆቴሎች ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ከ1 ሺህ 500 በላይ የሚኾኑ ሠራተኞች ከሥራ ውጭ መኾናቸውን በማሳያነት አንስተዋል፡፡
የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመቀናጀት በሰላሙ ዙሪያ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ እንደ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት ደግሞ የክልሉ ሕዝብ ለሰላም ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!