ባሕር ዳር: የካቲት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዋንዛዬ ፍል ውኃ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን በደራ ወረዳ በገዳም ገረገራ ቀበሌ ይገኛል። ሥፍራውን ለማግኘት መነሻዎትን ባሕር ዳር ከተማ አድርገው ወደ ጎንደር አቅጣጫ ሲጓዙ ወረታ ከተማ ለመድረስ ጥቂት ኪሎ ሜትር ሲቀርዎት ወደ ምሥራቅ የሚወስድን የጠጠር መንገድ ያገኛሉ። እዚህ ቦታ ላይ መውረድ ይጠበቅበዎታል።
በሥፍራው በርካታ ባለ ሦሥት እግር ተሽከርካሪዎች፣ የተወሰኑ ሚኒባስ ታክሲዎች፣ የጭነት መኪናዎች እና ሞተር ሳይክሎች ቁመው ይመለከታሉ። “ዋንዛዬ…ዋንዛዬ…” የሚሉ የረዳቶችን ድምጽም ወደቦታው ለመዳረስዎት ምልክት ነው።
በተሽከርካሪዎች አጠገብ ኾነው ወደ ፀሐይ መውጫ እና መግቢያ ሲመለከቱ አረንጓዴ ስጋጃ የተነጠፈበት የመሰለን ሰፋፊ ማሳ ይመለከታሉ። “አረንጓዴ ስጋጃ” የመሰለው ልምላሜ አርሶ አደሮች በመስኖ እያለሙት ያለ ሰብል ነው።
አካባቢው በበጋ እና በክረምት ሩዝ፣ ሽንኩርት ፣ በቆሎ … በስፋት ይለማበታል።
የቀንድ እና የጋማ ከብቶችም ሜዳው ላይ እንዳሻቸው እየፏለሉ ይግጣሉ። በአጠቃላይ አካባቢው ዓይነ ግቡ ነው። ወደ ዋንዛዬ በሚወስደው የጠጠር መንገድ ግራና ቀኝ የባሕር ዛፍ መመልከት ግድ ነው። በየቅርብ ርቀቱም የቆርቆሮ ቤቶች አሉ።
አሁን ቀልበዎትን ሰብስበው ከፈለጉ በባጃጅ አልያም በሚኒባስ ታክሲ ወይም በጭነት መኪና ወይም በሞተር ሳይክል መጓዝ ይችላሉ። 19 ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዙ በኋላም የዋንዛዬን ገጠር ቀመስ ከተማ ያገኛሉ። ከከተማዋ ወደ ግራ እጥፍ ብለውም ሁሉም ለማየት የሚጓጓለትን የዋንዛዬ የተፈጥሮ ፍል ውኃ ያገኙታል።
የዋንዛዬ ፍል ውኃ የሚገኝበት አካባቢ ቀደም ባለው ጊዜ የዋንዛ ዛፍ በስፋት ይገኝበት እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። በመኾኑም አካባቢው “ዋንዛዬ” ተባለ ባይ ናቸው። በዋንዛዬ ዙሪያ ገባው በ357 ሔክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ደን ይገኛል።
በአካባቢው በተለይ ሀገር በቀል እፅዋት ይበዙበታል። ለአብነትም ግራር፣ ዋርካ፣ ባምባ፣ ዋንዛ፣ ብሳና፣ እሼ፣ ዶቅማ፣ አባሎ፣ ዛና፣ላፍዲ፣አርቦጅ ከብዙ ጥቂቶቹ ሀገር በቀል ዛፎች ናቸው።
በዋንዛዬ የተፈጥሮ ደን ውስጥ ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ ድኩላ፣ ሚዳቋ፣ ከርከሮ፣ ጥንቸል፣ ሰሳ እና የመሳሰሉት እንስሳት እንደሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
ከዱር እንስሳቱ በተጨማሪ የተለያዩ የአዕዋፍት ዝርያዎችም በዋንዛዬ ይገኛሉ። ይኽም ዋንዛዬ በውስጡ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እንዳለው ይጠቁማል።
እንደ ደራ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት መረጃ የዋንዛዬ ፍል ውኃው እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስ ሙቀት አለው።
የአካባቢው ነዋሪዎች ከሥራ ውጪ በኾኑ ቀናት በፍል ውኃው ይዝናኑበታል። ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጣው የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ ከፍል ውኃው የፈውስ አገልግሎትን ፈልጎ ይጠቀማል።
የዋንዛዬ ፍል ውኃ አምስት ገንዳዎች አሉት። ገንዳዎቹ የወንድ፣ የሴት እና የቤተሰብ ተብለው ተከፋፍለዋል።
ተገልጋዩ ተራ አስከባሪ ሳያስፈልገው ወረፋውን ጠብቆ ይገለገላል።
የዋንዛዬ ፍል ውኃን ተጠቅመው ጎንዎን አረፍ ለማድረግ እና እህል ውኃ መቅመስ የሚችሉባቸው ቤቶች በቅጥር ግቢም ውስጥ ያገኛሉ። በተመጣጣኝ ዋጋም ግልጋሎት ይሰጣሉ።
ከዚህ ወጣ ብለውም የፈለጉትን አገልግሎቶችን የሚያገኙባቸው ቤቶችም እንዲሁ።
ስለ ተፈጥሮ ፍል ውኃ ሳይንስ ምን ይል ይኾን?
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ኮሌጅ ለዲደብሊው እንደገለጸው በተፈጥሮ ፍል ውኃ ተጠቃሚዎች ላይ ባደረገው ምርምር ከ80 በመቶ በላይ የሚኾኑት የፍል ውኃ ተጠቃሚዎች ለሕመማቸው መፍትሔ ማግኘታቸውን በሳይንሳዊ ምርምር ማረጋገጥ መቻሉን ገልጿል።
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!