ባሕር ዳር: የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መነሻዎትን ባሕር ዳር አድርገው ወደ አዴት ከተማ ሲሄዱ ሰባታሚት፣ ወንድአጣ፣ ቅምባባ እና ጉብሪት/ፈረስ ወጋ/ የሚባሉ ገጠር ቀመስ ከተሞችን አቆራርጠው ደብረ መዊዕ ከተማ ይደርሳሉ።
ከተማዋ በይልማና ዴንሳ ይዞታ ሥር ትተዳደራለች። ከባሕር ዳር ከተማ በ15 ኪሎ ሜትር ከአዴት በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። እዚች ከተማ ላይ ይወርዱ እና ወደ ምዕራብ አቅጣጫ በእግር 40 ደቂቃ ያህል እንደተጓዙ ግንብ ጊዮርጊስ ወይም የፋሲል ግንብን ያገኙታል።
በሌላ አቅጣጫ መነሻዎት ባሕር ዳር መድረሻዎትን መርዓዊ ከተማ አድርገው ወደ ምሥራቅ በኩል ሲጓዙ የብራቃት ከተማን ያገኛሉ። በዚህ በኩል ባለው የጠጠር መንገድ በመኪና ተጉዘው ፋሲል ግንብን ወይም ግንብ ጊዮርጊስን ማግኘት ይችላሉ።
በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ግንብ ቀበሌ ስለሚገኘው የፋሲል ግንብ ጥንታዊው ኪነ ሕንጻ ፍራንሲስ አንፍሬይ የተባሉ የውጭ ሀገር ጸሐፊ “ግንብ ጊዮርጊስ በአጼ ሱስንዮስ ዘመን የታነጸ የካቶሊክ ሚሲዮናውያን መኖሪያ ወይም የአጼው ወንድም ልዑል ሰዕለ ክርስቶስ መኖሪያ ነበር” በማለት ከትበዋል።
ኢትዮጵያዊው ጸሐፊ ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን ደግሞ ” አጼ ፋሲለደስ የባሕር ዳሩን የፋሲል ግንብ ቤተ መንግሥት አሰርተዋል” ባይ ናቸው። የግንብ ጊዮርጊስ ሌላ መጠሪያው “ፋሲል ግንብ” እንደኾነም ጨምረው አብራርተዋል።
በግንብ ጊዮርጊስ ሰፊ ግቢ ውስጥ በአራት ማዕዘን ቅርጽ የተገቡ ሦስት የፈራረሱ ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ቤቶቹ ምንአልባትም የንጉሡ ማረፊያ ቤት፣ የመኝታ ቤት እና የአንግዳ መቀበያ ቤት ሊኾኑ እንደሚችሉ ፍራንሲስ አንፍሬይ መላምታቸውን አስፍረዋል።
የንጉሱ ፈረስ ማሰሪያ፣ መመገቢያ እና ውኃ ማጠጫ ገንዳ እንዲኹም ማደሪያ ክፍሎች ዛሬ ድረስ አሻራቸው በጉልይ ይታያል። ሌላው ጉዳት ደርሶበት ግን ይዘቱን ሳይለቅ የሚገኝ የውኃ ማቆሪያ ገንዳ አለ:: ይህ ገንዳ በጎንደር እና ደንቀዝ እንደሚገኙት ምድር ውስጥ የተሠራ ሳይኾን በሕንጻ መልከ ከምድር በላይ የተሠራ ነው።
ከዚህ ቤተ መንግሥት በግምት 500 ሜትር ርቀት ላይ በጥድ እንጨት እና በድንጋይ ካብ የታነጸ ባለአራት ማዕዘን ቤተ ክርስቲያን እንደነበር የሚያመላክት የሕንጻ ፍርስራሽ አለ፡፡ ሦስት ክፍሎችም አሉት። መጀመሪያ ግንብ ማርያም ተብሎ ይጠራ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ።
በግንብ ጊዮርጊስ ከመሬት በታች የሚገኘው ኪነ ሕንጻ በልዩ ጥበብ በመታነጹ የጎብኝዎችን ቀልብ የመያዝ ኃይሉ ከፍተኛ ነው። ወደ ውስጥ ሲገቡም የሚታየው እጹብ ድንቅ የኪነ ሕንጻ ጥበብ መዳፍን አፍ ላይ ያስጭናል፡፡ በሦስት መስመር ተሰድረው በሚታዩት 21 አምዶች ላይ ያረፉት ቅርጻ ቅርጽም የዚህን ዘመን የኪነ ሕንጻ ውጤት ያስንቃሉ ባይናቸው ፍራንሲስ አንፍሬይ።
የግንብ ጊዮርጊስ ግድግዳ፣ ጣሪያ እና ቋሚ አምዶቹ የታነጹት ከድንጋይና ከኖራ ብቻ ነው፡፡ በባሕር ዳሩ ግንብ ጊዮርጊስ ወይም ፋሲል ግንብ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተለያዩ ቦታዎች ለየቅል የኾነ ስያሜዎችን ተችረዋል። ለአብነት “ጃን ገበር” ተብሎ የሚጠራ ግቢ አለ፡፡ “ግብር ሜዳ” የሚባልም እንዲኹ። “አጼ መዋኛ” ብለው የሚጠሩት የሰው ሠራሽ ባሕርም አለ፡፡
የግንብ ጊዮርጊስን ቤተ መንግሥት ዙሪያ ገባውን መቃኘት እና መጠበቅ የሚያስችሉ በእንቁላል ቅርጽ የተሠሩ እጹብ ድንቅ ማማዎችም አሉት፡፡ የግንብ ጊዮርጊስ እጅግ ማራኪ ከኾነ አምባ ላይ መገኘቱ የቤተ መንግሥቱ አሠራር ለማወቅ እና የዙሪያ ገባውን አስደሳች መልከዓምድራዊ ገጽታ ለመመልከት ምቹ ነው።
በግንብ ጊዮርጊስ ቀበሌ የተገነባው ዘመናዊ ትምህርት ቤት “ፋሲል ግንብ” ይባላል። ገበያው ደግሞ ግንብ ጊዮርጊስ በሚል ይጠራል። በግንብ ጊዮርጊስ ገበያ ቅዳሜ ዕለት የቀንድ እና የጋማ ከብት ይሸጥበታል። በሰርክ ደግሞ ማር ፣ ወተት፣ ቅቤ ፣ ጤፍ ፣ እንቁላል … ይገበያይበታል።
ዘጋቢ: ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!