ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መነሻዎትን ባሕር ዳር ከተማ አድርገው ወደ ጭስ ዓባይ ከተማ ሲሄዱ ሳባታሚት የምትባል ከተማን ያገኛሉ።ይህች ከተማ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደፈንድሻ ቆሎ እየፈካች እና አድማሷን እያሰፋች ያለች ከተማ ናት። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲው ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና ከፍተኛ የመሠረተ ልማቶች በከተማዋ ይገኛሉና ነው
ከተማዋ ቲማቲም፣ ድንች፣ ቃሪያ፣ በቆሎ፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ሽንኩርት በጋ እና ክረምት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጥባት የግብርና ውጤት ማዕከል የኾነች ከተማ ናት። ይችን ውብ ከተማ አልፈው እንደሄዱ ከባሕር ዳር 15 ኪሎ ሜትር ርቀት አካባቢ አንዳሳ ከተማን ያገኛሉ። አንዳሳ ስሟን ያገኘችው የዓባይ ወንዝ ገባር ከኾነው ከአንዳሳ ወንዝ ነው።
በጥንት ዘመን አንድ ሰው ከአንዳሳ ወንዝ ዓሣ ለማውጣት መቃጥኑን ይዞ ወደ ወንዙ ወረደ አሉ።
ከወንዙ ዳርቻ ላይ ኾኖም መቃጥኑን ወደ ወንዝ ይወረውራል። ቀኑን ሙሉ ውሎም አንድ ዓሣ ብቻ ይይዛል። ወደ ቤቱ ሲመለስም ጎረቤቶቹ “ሥራ እንዴት ነበር? ስንት ዓሳ አገኘኽ?” ብለው ጠየቁት። እሱም ፈዘዝ ብሎ “አንዳሳ ብቻ ይዤ ተመለስሁ” አላቸው ይባላል።
የሰውየውን ሐሳብ የሰማው ኹሉ በመገረምም በማዘንም “አንዳሳ… ” ማለቱን ቀጠለ። እነኾ እስከ ዛሬ ድረስም የከተማዋ ስያሜም አንዳሳ እንደኾነ ዘለቀ ይላሉ በከተማዋ የሚኖሩ አዛውንቶች።
አንዳሳ ላይ ወርደው ወደ ደቡብ አቅጣጫ የሽንብራ እሸት እየጠረጠሩ፣ ዘይቱና እና ማንጎ እየገመጡ፣ ሙዝና አገዳ እየበሉ ወዲህ የመስኖ ልማቱን እያደነቁ ለምለሙን የ’የሼማት’ ሜዳ ሰንጥቀው በእግር 50 ደቂቃ ያህል እንደተጓዙ ድንጋይ ደበሎ ማርያምን ያገኟታል።
ሌላው አማራጭ ደግሞ ከባሕር ዳር እስከ ጢስ ዓባይ ከተማ በመጓዝ ከከተማው የደቡብ ምዕራብ አቅጣጫን በመያዝ በመኪና ከቦታው መድረስ ይቻላል፡፡የድንጋይ ደበሎ ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተመሰረተችው በንጉሥ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት ከ1181 ዓ.ም እስከ 1221 ዓ.ም እንደኾነ የተለያዩ መዛግብት ይጠቁማሉ።
ቤተ ክርስቲያንዋ በላሊበላ ከተማ በሚገኙት ጥንታዊ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መልክ የታነጸች ናት።ድንጋይ ደበሎ የሚለው ስያሜ ከድንጋይ የተፈለፈለ መኾኑን ለመግለጽ “ድንጋይ ለብሶ ድንጋይ ተጎናጽፎ” ማለት እንደኾነ አባቶች ይናገራሉ።
ይህቺ ታላቅ የመስህብ ሃብት ቀደምት የሥልጣኔ አሻራቸውን ጥለው ባለፉት ጻድቁ ቅዱስ ላሊበላ አማካኝነት ከአንድ አለት ተፈልፍላ እንደተሠራች የአካባቢው ነዋሪ የኾኑ ቀደምት አባቶች ይናገራሉ፡፡
የቤተክርስቲያኗ መቅደስ ሙሉ በሙሉ ከድንጋይ የተፈለፈለ ኾኖ በአራት መዕዘን ቅርጽ በተሠሩ ስምንት ዐምዶች ተከፋፍሏል፡፡ ስምንቱ አምዶች አንዱ ከሌላው በመስቀል ቅርጽ የተገናኙ ናቸው።
ከዓለት ተፈልፍላ የተሠራችው ቤተ መቅደስ ሦስት በሮች አሏት። ግድግዳዋ እና ጣሪያዋ ከአንድ ወጥ ቋጥኝ ተፈልፍለው የተሠሩ ናቸው። ጣሪያዋ እጅግ በሚገርም ጥበብ የመስቀል፣ የከበሮ ቅርጽ እና በተለያዩ ሀረጎች ያጌጠ ነው።
በአንክሮ ለተመለከታት ከአንድ ወጥ ድንጋይ ከተፈለፈለው ጣሪያ ላይ ከበሮ ወደታች ተንጠልጥሎ እና የመስቀል ቅርጽ ተጋድሞ ማየት የሰው ልጅ በዚያ ዘመን ደርሶበት የነበረውን ሥልጣኔ አጉልቶ ያሳያል።
የመቅደሷ የግድግዳ ማዕዘኖች በጽዋ ቅርጽ የተሠሩ የጥበብ ውጤቶችን የሚያሳዩ ናቸው። በስተምስራቅ በኩል ከድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ የታቦት መንበርም ይገኛል።ሌላው አስገራሚ ነገር በመቅደሱ የውስጥ ወለል በእንጨት እና በድንጋይ የተዳፈኑ በርካታ ጉድጓዶች መገኘታቸው ነው።እነዚህ ጉድጓዶች የጥንታዊያን መንፈሳዊ አባቶች መቃብር ይኾናሉ የሚል ግምት አለ።
በቅዱስ ላሊበላ ከዓለት ተፈልፍሎ ከተሠራው ቤተመቅደስ በተጨማሪ በ17ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ፋሲል ከቤተ መቅደሱ ጋር በማያያዝ ባለ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሕንጻ አሠርተውበታል፡፡
ይህች ሕንጻ የተሠራችው ከድንጋይ እና ከጭቃ ኾኖ ከጣሪያው መገጣጠሚያ ሲደርስ በኖራ እና በድንጋይ ተሰርታለች፡፡በቤተ መቅደሱ መካከል አንድ ሜትር ተኩል አካባቢ የሚኾን ፍልፍል ድንጋይ አለ፡፡ ይህ ፍልፍል ድንጋይ አራት በሮች አሉት።
በሰሜን አንድ በር፣ በምዕራብ አንድ በር እና በደቡብ ሁለት በሮች ማለት ነው።የቤተክርስቲያኗ ጣሪያ ደግሞ ከእንጨት እና ከሣር የተሠራ ሲኾን ጣሪያው ያረፈው በምሥራቅ እና በሰሜን ምሥራቅ ከቋጥኙ ላይ በደቡብ፣ በሰሜን፣ በምዕራብ እና በምሥራቅ አቅጣጫ ያለው ደግሞ ያረፈው በቅድስቱ ግድግዳ ላይ ነው፡፡
ቅኔ ማኀሌቷ እንደ ማንኛውም ቤተክርስቲያን ከእንጨት መከታ የተሠራ ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ቤተክርስቲያን እጅግ በርካታ እና ውድ ቅርሶችን ከመያዟ በላይ የሰው ልጆችን የሥነ ሕንጻ ጥበብ የሚያሳይ ታላቅ የመስህብ ቦታ ናት፡፡
በእውነት የድንጋይ ደበሎ ውቅር አብያተ ቤተክርስቲያንን ጎበኙ ማለት 11ዱን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን የመጎብኘት ያህል ልዩ አድናቆት እና ስሜት ይሠጣል፡፡ድንጋይ ደበሎ ማርያም በሰሜን ጎጃም ዞን በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ በየመቃት ቀበሌ መገኘቷን ልብ ይሏል። የመረጃ ምንጮቻችን ድንቅ ምድር እና የኢትዮጵያ ታሪክ መጻሕፍት ናቸው።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!