‘’ማን ያሻግረኝ ብለሽ እንዳትጨነቂ፣ በጎባጢት ድልድይ በግንቡ ዝለቂ’’

0
360

ባሕር ዳር: መጋቢት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩ ቀደምት የንግድ ማዕከላት አንዷ በነበረችው የእንፍራንዝ ከተማ እና በታሪካዊው የጉዛራ ቤተ መንግሥት መካከል የጋርኖ ወንዝ ይገኛል፡፡ በቀደመው ጊዜ በዚህ ወንዝ ምክንያት የአፄ ሰርጸ ድንግል ባለቤት እቴጌ ሥነወርቅ ማርያም ከጉዛራ ወደ እንፍራዝ ልደታ ቤተክርስቲያን ለመሄድ እና ጸሎት ለማድረስ ይቸገሩ ነበር፡፡

ጉዛራ እና እንፍራዝ ከተማም በቅርብ ርቀት ማዶ ለማዶ ሆነው መተያየት ብቻ ነበር ግንኙነታቸው፤ በተለይም በክረምት ወቅት ወንዙን መሻገር የማይቻል ነበር፡፡ በመሆኑም እቴጌዋ በወንዙ ላይ ድልድይ እንዲሠራ አደረጉ፡፡
ዛሬ ድረስ ‘’ማን ያሻግረኝ ብለሽ እንዳትጨነቂ፣

በጎባጢት ድልድይ በግንቡ ዝለቂ’’ እየተባለ የሚዘፈንለት ድልድይም ተሠራ፡፡ የድልድዩ ስምም ጎባጢት ተባለ፡፡

የጎባጢት ድልድይ በአፄ ሰርጸ ድንግል ዘመን በ1560ዎቹ የተገነባ እንደኾነ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ ከ456 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው ድልድዩ ያለ አንዳች ብረት በኖራ አጣባቂነት ድንጋይን በድንጋይ በማነባበር የተሠራ ነው፡፡ የጎባጢት ድልድይ 12 ሜትር ርዝመት፣ ዘጠኝ ሜትር ቁመት፣ አራት ሜትር ስፋት እና አንድ ሜትር ውፍረት አለው፡፡ ግማሽ ክብ ሆኖ መሠራቱም ከባድ መጠነ ቁሶችን ለመሸከም አስችሎታል፡፡ የወቅቱን የሀገራችን የግንባታ ጥበብ ረቂቅነት ምስጢርም አጉልቶ ያሳያል፡፡

ከባሕር ዳር ጎንደር ከተዘረጋው አስፋልት 200 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የጎባጢት ድልድይ በስተሰሜን አቅጣጫ በጋራ የተከበበ እና ደቡባዊ ወሰኑ ደግሞ ለጣና ሐይቅ እጅግ የቀረበ ነው፡፡ ከቦታው የዕይታ አድማሳችንን ወደ ሰሜናዊ ምሥራቅ ካደረግንም ጥንታዊው የጉዛራ ቤተ መንግሥት በውስን እርምጃዎች የሚደረስበት መስሎ በቅርብ ርቀት ይታየናል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here