ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ነገሥታቱ እጅ የነሱበት፤ የክብራቸውን ዘውድ አውልቀው የተማጸኑበት፤ የከበረች አሻራቸውን ያስቀመጡበት፤ ድንጋይ እንደ እንጨት በሚሥማር የተመታበት፤ ተመትቶም የጸናበት፤ ታላላቆቹ የተሰባሰቡበት፤ ሊቃውንቱ የተጠለሉበት፣፤ ሳይቋረጥ ምሥጋና የሚቀርብበት፤ ቅዱሳኑ የተመላለሱበት፤ የረቀቀ አሻራ ያስቀመጡበት ሥፍራ፡፡
የረዘመ ታሪክ የሚነገርለት፤ የገዘፈ ታሪክ የሚነበብበት፤ የነገሥታቱ አሻራ ከፍ ብሎ የሚታይበት፤ ሊቃውንቱ እውቀትን የሚዘሩበት፤ ደቀመዛሙርቱ አብበው አፍርተው የሚታዩበት፡፡ የቤተ መንግሥቱ እና የቤተ ክህነቱ ጥበብ የተባበረበት፤ መኳንንቱ እና ሊቃውንቱ በአንድ ላይ የሚከትሙበት፤ ስለ ምድር ሰላም፣ ስለ ሕዝብም ፍቅር የሚማጸኑባት ታላቅ ቦታ፡፡
የንጉሥ ሚካኤል ታሪክ ሲታሰስ፣ የእርሳቸው አሻራ ሲታወስ አብሮ ይታወሳል፤ ከፍ ከፍ እያለ ይነሳል፤ ፍቅር፣ ሰላም እና አንድነት የማይጠፋበትን ከተማ በታሪክ ካስዋቧት፣ በሃይማኖት ካከበሯት፤ በኪነ ሕንጻ ካስጠሯት፤ በጥበብ ካላቋት፤ በእውቀት ካረቀቋት የከበሩ ሥፍራዎች መካከል አንደኛው ነው፡፡ ደሴ ርእሰ አድባራት ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን፡፡
እድሜ የጠገቡት አጸዶች ለአጀብ የሚያረገርጉ፣ ለምሥጋና ጉምብስ ቀና የሚሉ ይመስላሉ፡፡ አንደበት ኖሯቸው የሚናገሩ፣ የዚያን ታላቅ ደብር ታሪክ እና ምስጢር የሚመሰክሩም ይመስላሉ፡፡ ጸጥታ የመላበት፣ አምላካቸውን የሚማጸኑ ምዕመናን የማይታጡበት ቅዱስ ስፍራ ነው፡፡
ታሪክ ባከበረው በዚያ ታላቅ አጸድ ሥር ተገኘን፡፡ ከአባቶች ታሪክ ሰማሁ፡፡ በደሴ ርዕሰ አድባራት ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን መምህር ተስፋማርያም ቢሰጠኝ እና የዝማሬ መዋሲት መምህር እና የሕግ ክፍል ኀላፊ ሊቀ መዘምራን አክሊሉ ሐረገወይን ረጅሙን ታሪክ ነግረውናል፡፡
ይህ ቅዱስ ሥፍራ አስቀድሞ ገና በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አበው ጸሎት የሚይዙበት፣ ሱባኤ የሚገቡበት እና አበው የሚኖሩበት ነበር፡፡ ታላላቆቹ እና ቅዱሳኑ አባቶች እነ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ፣ እነ አቡነ ተክለሃይማኖት፣ እነ አቡነ ዜና ማርቆስ ሱባኤ ይይዙበት፣ ጸሎት ያደርሱበት እንደነበር ነግረውናል፡፡ ታላቁ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘ ጋስጫ ሆኅተ ብርሃን የተሰኘውን ድርሰታቸውን በዚሁ ሥፍራ ላይ እንደደረሱበትም ይነገራል፡፡
መነሻው ቀደም ያለ እና የረቀቀ ታሪክ ያለው ነው፡፡ በዚህ ቅዱስ ሥፍራ በአጼ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት የተሠራ ቤተ ክርስቲያን እንደነበረበትም ይነገራል፡፡ ምሥጋናው ታደሰ (ዶ.ር) “ሚካኤል ንጉሠ ወሎ ወትግሬ” በተሰኘው መጽሐፋቸውም ይሄን ታሪክ ጽፈውታል፡፡ በአጼ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት የተሠራው ሥራ ከግራኝ አሕመድ ጋር በተደረገው ጦርነት ዘመን እንደፈረሰ ተከትቧል፡፡
ዘመን አልፎ፣ አዲስ ዘመን መጣ፡፡ በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ ነገሥታቱ እየተቀያየሩ ምኒልክ በዙፋኑ ላይ ተቀምጠውበት ነበር፡፡ ንጉሡ አልገብር ያለውን እያስገበሩ፤ ያልተደላደለውን እያደላደሉ፤ ጠንካራ ሀገር፤ አስፈሪ ዙፋን እያጸኑ ነበር፡፡ ተክለጻዲቅ መኩሪያ በታሪክ መጻሕፋቸው ዳግማዊ ምኒልክ የእሳቸውን እና የእቴጌ ጣይቱን የንግሥና በዓል በወረኃ ጥቅምት አክብረው በወረኃ ታኅሣሥ ወደ ትግራይ ጉዞ ጀመሩ፡፡ በታኅሣሥ ዘጠኝ ከእንጦጦ ወደ ትግራይ ለመሔድ ጉዞ ጀምረው በታኅሣሥ 27 ቀን ደሴ ገቡ፡፡ በደሴ የልደትን እና የጥምቀትን በዓል ካከበሩ በኋላ ደሴ ላይ እቴጌ ጣይቱን ትተው ጉዟቸውን ቀጠሉ ብለዋል፡፡
ዘመን ሲያገጣጥም ደሴ የገቡበት ቀን ወር በገባ በ27ተኛው ቀን ደብሩም መድኃኔዓለም፡፡ ዶክተር ምሥጋናው ደግሞ አጼ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ከኾኑ በኋላ ሀገር ለማደላደል እና ለማስገበር ወደ ትግራይ በዘመቱ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ እስከደሴ ድረስ አብረዋቸው ተጉዘው ነበር፡፡ በኋላም ደሴ ላይ ቀሩ፡፡ ራቅ ብሎ ዘመን የሚቆጠርለት ታላቁ እና ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ንጉሠ ነገሥቱ ትግራይ ደርሰው እስኪመለሱ እቴጌዋ በዚህ ቅዱስ ሥፍራ መቃረቢያ ሰርተው ታቦተ መድኃኔዓለምን አስገቡ በማለት ጽፈዋል፡፡
አበው ሲነግሩን “ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ሰሜኑን አደላድለው እስኪመለሱ ድረስ እተጌ ጣይቱ በደሴ ተቀመጡ፡፡ በዚህም ጊዜ ሥፍራውን ተመለከቱት፡፡ ባዩትም ጊዜ ደስ ተሰኙ፡፡ በዚህም ሥፍራ መቃረቢያ አሠርተው ታቦተ መድኃኔዓለምን አስገቡ፡፡ ለዚህም ማስረጃ ይኾን ዘንድ የወርቅ ወንጌል አጽፈው ለቤተ መቅደሱ ሥጦታ ሰጥተዋል” ነው ያሉን፡፡ እንደ አበው ቃል ሁሉ የታሪክ ጸሐፊው ዶክተር ምሥጋናውም እቴጌ ጣይቱ ለቤተክርስቲያኑ ብራና ወንጌለ ዘወርቅ አበርክተዋል፤ በዚህም በምኒልክ መንግሥት፣ በሚካኤል መስፍንነት፣ እቴጌ ጣይቱ ደሴ መድኃኔዓለምን ሲሠሩ አለቃ ገበዙ አለቃ ኃይሌ ናቸው የሚል ጽሑፍ ሠፍሮበታል ብለው ጽፈዋል፡፡
ምኒልክ የሰሜኑን የሀገራቸውን ክፍል አደላድለው፤ ያልገበረውን አስገብረው፤ የገባውን ይቅር ብለው፤ ሹመው ሸልመው ተመለሱ፡፡ ጊዜውም ነጎደ፡፡ የዚያኔው ራስ ሚካኤል የኋላው ንጉሥ ሚካኤል ደብር ሊያስደብሩ፣ አጸዱንም ሊያሳምሩ ወደዱ፡፡ አስቀድመው ከንጉሥ ምኒልክ እጅ የተቀበሉትን የጊዮርጊስን ቤተ መቅደስ ሊያሠሩ ፈለጉ፡፡
አበው እንደሚሉት ይህ የአምላክ ፈቃድ ነው፡፡ የታዘዙት ለቢለን ጊዮርጊስ የሚያስቀምጡት ግን ለመድኃኔዓለም ነበር፡፡ ሚካኤል አስቀድመው የቢለን ጊርዮርጊስ ሕንጻ ቤተክርስቲያንን አስጀመሩ፡፡ ቀን ሲሠራ ይውላል፡፡ ሌሊት ተንዶ ያድራል አሉ፡፡ በዚህም ተግባር ሚካኤል ይጨነቁ ነበር፡፡ የሚያስጨንቃቸውን ያቀሉላቸው፤ የተቋጠረውን ምስጢርም ይፈቱላቸው ዘንድ በዘመኑ ለነበሩ ታላቅ ባሕታዊ ነገሯቸው፡፡ “የሰማዕቱን ቤት ልሠራ ብዬ እየተናደ አስቸገረኝ፡፡ አምላኬ ተቀይሞኝ ይኾን? ምን ላድርግ” አሏቸው፡፡ ባሕታዊውም ደብሩን ከማስደበራቸው አስቀድመው ሱባኤ ይይዙ ዘንድ ነገሯቸው፡፡
የቀደሙት ነገሥታት፣ መሳፍንት እና መኳንንት ምስጢር በተሰወረባቸው፣ ጥበብ በተጋረደባቸው ጊዜ ወደ አምላካቸው ያመለክታሉ፡፡ በጾም እና በጸሎት ይተጋሉ፡፡ ሚካኤልም እንደተባሉት ሁሉ ሱባኤ ያዙ፡፡ ሱባኤ በያዙ በሰባተኛውም ቀን “መጀመሪያ የንጉሡን፣ የፈጣሪውን የጌታውን ቤት ሥራ፤ ከዚያም ቀጥለህ የእርሱን የአገልጋዩን ቤት ትሠራለህ” የሚል ታላቅ መልስ እና መመሪያ አገኙ፡፡ እንደተባለው አደረጉ፡፡
ሚካኤል ቤተ ክርስቲያኑን ያሠሩ ዘንድ ማስቆፈር ጀመሩ፡፡ በተቆፈረም ጊዜ የሕንጻ ቤተክርስቲያን ፍርስራሽ ተገኘ፡፡ ከሕንጻ ፍርስራሹ ጋርም አንድ የብረት መስቀል ተገኘ ነው ያሉኝ አበው፡፡ ያን ያማረ እና የተዋበ ቤተክርስቲያንም ማሳነጽ ጀመሩ፡፡ አሳምረው ያሳንጹበት ዘንድም ድንጋይ፣ እንጨት፣ ሣር፣ ኖራ እና የሥንዴ ዱቄት መረጡ፡፡ ዶክተር ምሥጋናውም በታሪክ መጽሐፋቸው ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ በድንጋይ፣ በኖራ፣ በስንዴ ዱቄት የተሠራ ነው፡፡ አሸዋው እና ድንጋዩ ከቦርከና እና ከገራዶ ወንዞች፤ እንጨቱ ከአልብኮ ሳልመኔ ከተባለ ሥፍራ እንደመጣም ይነገራል ብለው ጽፈዋል፡፡
ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ በተሠራበት ዘመን ከአረብ ሀገራት፣ ከሕንድ፣ ከጀርመን እና ከግሪክ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የሥነ ሕንጻ እና የምሕንድስና ባለሙያዎች በብዛት የሚገኙበት ዘመን ስለነበር ራስ ሚካኤል ሌንዳ የተባለውን ግሪካዊ መሐንዲስ መርጠው ሥራውን ማሠራታቸው ይነገራል፡፡ አሠራሩ እጀግ ያማረ እና የረቀቀ ነው ይላሉ አበው፡፡ በዚያ ዘመን የተሠራው ያማረ ቤተ መቅደስ እድሳት ሳይደረግለት፤ ውበቱ እና ግርማው ሳይደበዝዝበት ዛሬም ድረስ አለና፡፡
ይህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በሚሠራበት ዘመን አንድ ክስተት ተፈጠረ፡፡ ለደረጃ የተመረጠች አንዲት ጥርብ ድንጋይ ተሠበረች፡፡ ሠሪዎቹም የድንጋዩዋን መሠበርም ለሚካኤል ነገሩ፡፡ ንጉሥ ሚካኤልም በሚሥማር ምታት ብለው አዘዙ አሉ፡፡ የታዘዘውንም አደረጉ፡፡ ድንጋዩም በሚሥማር ጸና፡፡
ደሴ መድኃኔዓለም ድንጋይ በሚሥማር የጸናበት ተብሎ ይነገራል፡፡ ስለዚህ ክስተት የታሪክ ሰዎች ጽፈዋል፡፡ አበውም ይናገራሉ፡፡ እኔም በዓይኔ ተመልክቼ ተደንቄያለሁ፡፡ ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ በወረኃ ጥር 1905 ዓ.ም ተጀምሮ በወረኃ ሚያዚያ ተጠናቀቀ፡፡ ያን የመሠለ የረቀቀ ቤተ መቅደስ ለመሥራት ሦስት ወራት ከ14 ቀናት ብቻ አስፈልገዋል፡፡ ይህም ድንቅ ነውና ሲነገር ይኖራል፡፡ በሦስት ወራት ከ14 ቀናት የታነጸው ቤተክርስቲያን ዛሬም ድረስ ከእነ ክብሩ እና ከእነ ማዕረጉ አለ፡፡
ሌላም ታሪክ አለው አለቃ ደስታ የተባሉ ታላቅ ሰዓሊ በቤተ መቅደሱ ስዕል ሳሉ፡፡ ይህም ስዕል ለመሳል እንደ ሕንጻው ሁሉ ሦስት ወራት ከ14 ቀናት ብቻ ነው ያስፈለገው ብለውናል አበው፡፡ ይሄን ነገር ምን ይሉታል? ይሄን ጥበብ እና ይሄን ድንቅ ሥራ ምን ብለው ይገልጹታል? ግሩም ብሎ ከማለፍ በስተቀር፡፡ በወረኃ ሐምሌ በዕለተ መድኃኔዓለም ቀን ቅዳሴ ቤቱ ከበረ፡፡ ይሄም ታሪክ ዛሬም ድረስ እየታሰበ እና እየተከበረ መቀጠሉን አበው ነግረውናል፡፡
ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ በሚሠራበት ዘመን ንጉሥ ሚካኤል በዚያው ድንኳን ጥለው ያሠሩ እንደነበር ይነገራል፡፡ ምን ይሄ ብቻ እሳቸውም ይሠሩ ነበር ይባላል፡፡ ንጉሡ ደብር ተደብሮ ቅዳሴ ቤቱ ከተከበረ በኋላ እግዚአብሔር ለመረጠው፣ ላከበረው እና ለቀደሰው ሥፍራ ምን ላድርግ ብለው ተጨነቁ አሉ፡፡ በታላቁ ደብር የሚያገለግሉ ሊቃውንትንም ከአራቱም ማዕዘን አስፈለጉ፡፡ በአራቱም ማዕዘን አሽከር ልከው ሊቃውንትን ሰበሰቡ፡፡ እርስት ጉልትም ሰጥተው ሳያስታጉሉ እያገለገሉ ይኖሩ ዘንድ ሊቃውንቱን አኖሩ፡፡ ንጉሡ የሠጡት እርስት እና ጉልት በደርግ ዘመን እሰኪወረስ ድረስ አብሮ ዘልቆ ነበር፡፡
ይህ ታላቅ ደብር ከሦስት መቶ በላይ አገልጋዮች የነበሩበት፤ ታላላቅ ሊቃውንት የነበሩበት፣ ባሕታውያን የተመላለሱበት፤ ዛሬም ባሕታውያን ያልነጠፉበት ታላቅ ሥፍራ ነው ይላሉ አበው፡፡ ዛሬም ከመቶ በላይ አገልጋዮች ያሉበት ታላቅ ደብር እንደኾነ ሰምተናል፡፡ ግሸን ደብረ ከርቤ ላይ ያረፈው ግማደ መስቀሉ ወደ ግሸን ከመውጣቱ አስቀድሞ በዚያ ቅዱስ ሥፍራ አርፎ እንደነበርም ይነገራል፡፡
አበው እንደነገሩን በደሴ ርእሰ አድባራት ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በሰርክ የኪዳን እና የቅዳሴ ቃለ እግዚአብሔር አይታጉልበትም፡፡ ይህ ከዓመት አስከ ዓመት ጀምበር ጠልቃ በዘለቀች ቁጥር ሲደረግ የኖረ፣ እየተደረገም ያለ ነው ይላሉ፡፡ ጥበብ እና መንፈስ ያልተለየበት፣ የአምላክ ምሥጋና የማይለይበት ቅዱስ ሥፍራ ነው፡፡
ምሥጋናው ታደሰ (ዶ.ር) “ሚካኤል ንጉሠ ወሎ ወትግሬ” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደጻፉት ንጉሥ ሚካኤል በደሴ ከተማ አራት አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸዋል፡፡ እነርሱም የመድኃኔዓለም፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የቅድስት ማርያም እና የአቡ ተክለሃይማኖት አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ በርካታ የንጉሡ አሻራዎች ካሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል የደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አንዱ ነው፡፡
ወሎየዎች የሚያርፉበት፣ የሚጠለሉበት፣ በረከት የማይታጣበት፣ እውቀት እና ቃለ እግዚአብሔር እንደ ጎርፍ የሚፈስስበት ነው ይላሉ አበው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ታሪኩን እንዲያውቁት፣ እንዲያደንቁት፣ ታሪኩን አውቀው እንዲጠብቁትም አበው ጠይቀዋል፡፡ ሊቃውንት እንዲፈልቁበት ጥበቃ ያስፈልገዋል ይላሉ።
በዚህ የከበረ ሥፍራ ታሪክ ያከበራቸው ቅርሶች መኖራቸውን አበው ነግረውናል፡፡ በዚህ ታላቅ ሥፍራ የንጉሥ ሚካኤል አልባሳት፣ የራስ ዘውዶች፣ አልጋ፣ መቀመጫ ወንበር፣ የብራና መጻሕፍት፣ መስቀሎች እና ሌሎች ንዋየ ቅድሳት እንደሚገኙበት ዶክተር ምሥጋናው ጽፈዋል፡፡
የታሪክ መዝገብ ብራናው፤ የጥበብ መፍለቂያ የከበረ ቦታው፤ የሊቃውንቱ መቀመጫ ተራራው ርእሰ አድባራት ደብረ መድኃኔት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን፡፡ ደሴ ተደረሶ ሳይጎበኙ የማይመለሱበት ቦታ ነው።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!