”የሰላም እጦት የጎብኚዎችን እንቅስቃሴ ገድቧል” የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ

0
297

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም እጦት የጎብኚዎችን እንቅስቃሴ ገድቧል ሲል የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ ቅርስን በመጠበቅ፣ በመንከባከብ እና በመጠገን ዙሪያ ባሉ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ ዓባይ ቅርስን በመጠበቅ፣ በመንከባከብ እና በመጠገን ለጉብኝት ምቹ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ የማሳደግ ሥራ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በዚህም የመንግሥት በጀት እና የኅብረተሰብ ተሳትፎን በማቀናጀት፦
👉 በ2015 በጀት ዓመት በ17 ሚሊየን ብር ለ32 ቅርሶች፣
👉 በ2016 በጀት ዓመት በ74 ሚሊየን ብር ለ39 ቅርሶች ጥገና እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲታወቁ፣ ለጉብኝት፣ ለጥበቃ፣ እና ለእንክብካቤ ምቹ እንዲኾኑ መሠራቱንም አቶ አባይ ገልጸዋል።
የጎብኝዎችን መዳረሻ የማልማት፣ የመንከባከብ እና የማስተሳሰር ሥራም መሠራቱን ነው ምክትል ኀላፊው የጠቀሱት። ደሴን ማዕከል ያደረገ አይጠየፍ ቤተ መንግሥት፣ ሎጎ ሐይቅ፣ ወረኢሉ ፣ውጫሌ፣ ይስማ ንጉስ እስከ ላሊበላ የሚተሳሰር የቱሪስት መዳረሻ ጥገና እና እንክብካቤ ሥራንም በአብነት ጠቅሰዋል።
በ2016 በጀት ዓመት የጎብኚዎች ፍሰትን በተመለከተም፦

👉 የሀገር ውስጥ ጎብኚ 7 ሚሊየን ታቅዶ 5 ሚሊየን፣
👉 የውጪ ሀገር ጎብኚ 31 ሺህ 814 ታቅዶ 17 ሺህ ብቻ መጎብኘታቸውን አብራርተዋል። ላሊበበላ፣ ጎንደር፣ የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርኮ፣ ጣና እና ዙሪያውን እንዲሁም ሃይማኖታዊ በዓላት በዋናነት የተጎበኙ መስህቦች ናቸው።
በሠላም ችግሩ ምክንያት የውጪ ጎብኚው የቀነሰ መኾኑን የጠቀሱት አቶ አባይ ሠላም ቢኾን ኖሮ እቅዱ የሚሳካበት እና ከቱሪዝም የሚገኘው ሁለገብ ጥቅም ከፍ ይል እንደነበር ነው የጠቀሱት።
በገቢ በኩልም፦

👉 ከሃገር ውስጥ ጎብኝዎች 4 ቢሊየን ብር ታቅዶ 2 ነጥብ 37 ቢሊየን ብር፣
👉 ከውጪ ሀገር ጎብኝዎች 190 ሚሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 66 ሚሊየን ብር ብቻ ገቢ መገኘቱን አቶ አባይ ጠቅሰዋል።
የቱሪዝም ዘርፉ ከጫማ ማሳመር እስከ ትራንስፖርት እና ሆቴል አገልግሎት ድረስ ግብይት የሚፈጸምበት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መኾኑን ምክትል ኀላፊው ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ ዘንድሮ በክልሉ በተከሰተው የሠላም እጦት ምክንያት ዝቅተኛ የጎብኝዎች ፍሰት እና የገቢ መጠን መታየቱን ገልጸዋል።
ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና ከሰሜኑ ጦርነት ጫና አገግሞ ለወራት መነቃቃት ታይቶበት የነበረው የአማራ ክልል የቱሪዝም ምጣኔ ሃብት አሁን ባለው የውስጥ ግጭት ምክንያት መልሶ መዳከሙን ነው ምክትል ኀላፊው የተናገሩት።

ቢሮው የቱሪዝም ምጣኔ ሃብቱ እንዲነቃቃ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መሥራቱን እንደሚቀጥል ኀላፊው ተናግረዋል። ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግም ኅብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here