“ጎብኝ ጠባቂ ወገኖች፤ እንግዳ የናፈቁ ዐይኖች”

0
286

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከበርሃው ዘብ ከአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ሰማይን ተደግፎ የቆመ እስከሚመስለው ራስ ደጀን ተራራ ድረስ ያማሩ እና የተዋቡ ሥፍራዎች ያሉበት፣ ተፈጥሮ ውበትን የገለጠችበት፣ ባሕል እና ታሪክ ገዝፎ የሚኖርበት፣ ያልተበረዘ ማንነት የሚገኝበት፣ የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ግዮን (ዓባይ) የሚፈልቅበት፣ የተንጣለለው የጣና ሐይቅ ያለበት፣ ጠቢባን መርምረው ያልጨረሷቸው የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ረቅቀው የታነጹበት፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታት እና ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት የሚያሳምሩት ክልል ነው።

ከአንደኛው ንፍቅ ወደ ሌላኛው ንፍቅ በተንቀሳቀሱ ቁጥር የበዙ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች የመሉበት፣ ባሕል እና እሴት የበዙለት፣ እርምጃ እየለኩ በተጓዙ ልክ በእርምጃው ወሰን ድንቅ ነገር የሚያገኙት ነው። በሻዳይ፣ በአሽንድዬ እና በሶለል ውበት፣ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ እሴት እና ባሕል የሚገለጡበት፣ በቡሄ ባሕል እና ታሪክ የሚጣመሩበት፣ በሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ጥንታዊት፣ ሃይማኖት አክባሪነት፣ ሥርዓት ጠባቂነት የሚታይበት ክልል ነው የአማራ ክልል።

በአራቱም ንፍቅ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ታላላቅ ጎብኝዎች ኹሉ ሊያዩት የሚመኙት፣ ባዩትም ጊዜ የሚደሰቱበት ነው። ለጉብኝት ሰላም ቀዳሚው ጉዳይ ነውና ሀገር ሰላም ሲኾን ክልሉን ለማየት የሚገሰግሱት በርካቶች ናቸው። የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ ችግሮች ግን ጎብኝዎች ወደ ክልሉ እንዳይመጡ አድርገዋል። ጎብኝዎች ባለመምጣታቸው የቱሪዝም ገቢ ቀንሷል። ገቢ በመቀነሱ ምክንያት ደግሞ በቱሪዝም ገቢ የሚተዳደሩ ወገኖች ተጎድተዋል። አሁን ላይ “ጎብኝ ጠባቂ ወገኖች፤ እንግዳ የናፈቁ ዐይኖች” በርካታ ናቸው።

ታደሰ ዘላለም ይባላል። በጣና ሐይቅ የባሕር ትራንስፖርት በግል ጀልባዎች ማኅበር የጀልባ ካፒቴን ነው። ሰላም በኾነ ጊዜ የጣና ገዳማትን ለመጎብኘት፣ በጣና ሐይቅ ላይም በጀልባ እየተንቀሳቀሱ ደስታን ለማግኘት ለሚመጡ ጎብኝዎች የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ገቢ ያገኛል። ሰላም በሌለ ጊዜ ግን ጎብኝዎች ይቀራሉ። “ቱሪዝም ሰላም ይፈልጋል” የሚለው ታደሰ ሰላም በነበረበት ወቅት በቀን እስከ ሦስት ጊዜ በጣና ሐይቅ ውስጥ በሚገኙ ገዳማት ደርሶ መልስ ሲሠራ እንደነበር አስታውሷል።

ከኮረና ቮይረስ ወረርሽኝ መከሰት ጀምሮ ባሉት ዓመታት ግን ቱሪዝሙ ፈተና ገጥሞታል ነው የሚለው። ሀገር ሰላም ኾኖ ቱሪዝም የሚመለስበትን መንገድ እየናፈቅን ነው ብሏል። በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ይባስ ብሎ ሥራ ጠፍቷል፣ ወደ ደሴቶች አልፎ አልፎ የሚደረግ ጉዞ ካልኾነ በስተቀር ሥራ የለም፣ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ፍሰት በጣም ጥቂት ነው፣ በወር ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ሊመጡ የሚችሉበት እድል አለ ይላል። ከቱሪዝም የማይጠቀም የለም የሚለው ታደሰ አሁን ላይ በደህናው ጊዜ ያጠራቀምናትን ጥሪት እየተጠቀምን ነው እንጂ ገቢ የለንም ነው ያለው።

ሥራችን በባሕሪው ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት አመች አይደለም፣ ምክንያቱም ጎብኝ ይመጣል ብለን ስለምናስብ የሥራ ቦታችን አንለቅም፣ አገኘንም አጣንም ቦታውን አንለቅም፣ አሁን ላይ እንደምንም ተቸጋግረን ነው ያለነው ብሏል። ሰላም ሲጠሩት በራሱ ምቾት ይሰጣል፣ ሰላም ከሌለ ለመሥራት አይደለም ወጥቶ ለመግባት አይቻልም፣ ሰላም ትልቅ ነገር ነው፣ ምኞታችንም ፍላጎታችንም ሰላም እንዲኾን ነው፣ ሰላም ከራስ ይጀምራል፣ ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ በመኾኑ፣ ሁሉም ለሰላም አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት ይላል።

የባሕር ዳር እና አካባቢው አስጎብኝዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ማስታዋል ዘለቀ የአማራ ክልል ቱሪዝም ከኮረና ቮይረስ ወረርሽኝ እና ከሕወሓት ወረራ ማግስት መነቃቃት አሳይቶ እንደነበር አስታውሰዋል። በተለይ በ2015 ዓ.ም የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች በሥፋት ይመጡ ነበር ነው ያሉት። አሁን ላይ በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ቱሪዝሙ በእጅጉ ተጎድቷል ይላሉ።

እንቅስቃሴያችን ከጎብኝዎች ጋር ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ የሀገር ሰላም ውሎ ማደርን፣ የጎብኝዎች መንቀሳቀስን እንፈልጋለን ነው ያሉት። በአማራ ክልል የጎብኝዎች እንቅስቃሴ ከፍ በሚልባቸው ወራት የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ያሰቡትን እንዳያሳኩ እንዳደረጋቸውም ገልጸዋል። ብዙ ጠብቀን አልተሳካልንም፣ አሁን ላይ በጫና ውስጥ ነን፣ ሥራችን ከጨዋታ ውጭ ኾኗል፣ በቱሪዝም ገቢ ቤተሰቦቻቸውን የሚያሥተዳድሩ የማኅበሩ አባላት ችግር ስለ ገጠማቸው ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት እየተገደዱ ነው፣ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው ብለዋል። የኑሮ ውድነት ከገቢ ማጣት ጋር ተደራርቦ ሕይወትን አክብዶታል ነው ያሉት። በሰላም እጦት ቀጥተኛ ገፈት ቀማሾቹ እኛ ነን ብለዋል።

ለቱሪዝም እንቅስቃሴው መመለስ ሰላም ወሳኙ ጉዳይ ነው፣ ጦርነት የትም ሀገር ይኖራል፣ ነገር ግን መጨረሻው የሰላም ስምምነት ነው፣ ከእኛ ሀገር ግን ስንት ሰው ከሞተ በኋላ ስምምነት ሊደረግ እንደኾነ አላውቅም ነው ያሉት። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት በክልሉ ያለው የሰላም እጦት ለሥራው እንቅፋት እንደኾነበት አስታውቋል። በክልሉ 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ይጎበኙታል ተብሎ ታቅዶ 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ጎብኚዎች እንደጎበኙት ነው የተገለጸው። ከእቅድ እንጻር 91 ነጥብ 5 በመቶ ነው ተብሏል። 31 ሺህ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ይጎበኙታል ተብሎ ታቅዶ 17 ሺህ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እንደጎበኙት በግምገማው ተመላክቷል።

ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች 4 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱም ተገልጿል። ከውጭ ሀገር ጎብኚዎች ከ190 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ 66 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱም ተመላክቷል። በአጠቃላይ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱ ነው የተመላከተው። በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር ለቱሪዝም ገቢ ማነስ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ተብሏል። የፀጥታ ችግሩ በእቅድ የተያዙ ሥራዎችን ለመሥራት አስቸጋሪ ኾኖ መቆየቱም ተገልጿል። በአንዳንድ አካባቢዎች ንብረቶች መዘረፋቸው በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለመግባት አስቸጋሪ መኾኑንም ተመላክቷል።

ቢሮው በችግር ውስጥ ኾኖ በዘርፉ ከ7 ሺህ 110 በላይ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል። ከ16 ሺህ 250 በላይ ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ናቸው። በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በዘጠኝ ወራቱ ያልተከናወኑ ችግሮችን በቀጣይ ጊዜያት መሥራት እንደሚያስፈልግም ተገልጿል። ንብረታቸው የተዘረፉባቸውን ተቋማት በመደገፍ እና ክትትል በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ይጠበቃል ነው የተባለው።

ገቢያቸውን በቱሪዝም ላይ ያደረጉ እና በገቢ መቀነስ ምክንያት የተቸገሩ ወገኖችን በየአካባቢው መሥተዳድሮች ድጋፍ ማድረግ እና አማራጮችን ማመላከት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል። ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ወሳኙ ጉዳይ ሰላም በመኾኑ ለሰላም መሠራት እንደሚገባም ተመላክቷል። ቢሮው ግጭቶች በባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት እንዲፈቱ፣ በውይይት እልባት እንዲያገኙ መሥራቱም ተገልጿል። የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ችግሮች በውይይት እና በሽምግልና እንዲፈቱ እንዲያግዙ ቢሮው ሲሠራ መቆየቱን እና አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል። የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ችግሮች ሁሌም በባሕላዊ የእርቅ ሥርዓት እንዲፈቱ እንደሚሠራም ተገልጿል። ነገር ግን አንዳንድ ግጭቶች ከአቅም በላይ ይኾናሉ ነው የተባለው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here