እንደ መልካም እስክስታ ወራጅ የሚውረገረገው የየጁቤው ውርግርግ ዋሻ!

0
211

ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የየጁቤው ውርግርግ ዋሻ የፏፏቴ እና የድልድይ የወል መጠሪያ ነው። ይህ ፏፏቴ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በባሶሊበን ወረዳ ይገኛል። “ውርግርግ ፏፏቴ” ወይም “ውርግርግ ዋሻ” ወይም “የእዜር ድልድይ” በሚል ስምም ይጠራል። ፏፏቴው ከወረዳው ዋና ከተማ የጁቤ 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ደንደገብ ቀበሌ ጠጀሽ ደነብ እና ዳምሽ በሚባሉ ሁለት ጎጦች መካከል ይገኛል።

የየዳ እና የበረደና ወንዞች ከተለያዩ አካባቢዎች ተነስተው ለየቅል እየተጠማለሉ መሥመራቸውን ይዘው ይፈሳሉ። እነዚህ ወንዞች እዚህ ቦታ ላይ ሲደርሱ ተቀላቅለው የውርግርግ ፏፏቴ ይፈጥራሉ። ፏፏቴው 25 ሜትር ያህል ቁልቁል ሲወረወር የሚረጨው ፍንጣቂ የተነደፈ ጥጥ የሚመስል ጉም ይፈጥራል። ይህም አካባቢውን የተለየ ግርማ ሞገስ ያጎናጽፈዋል።

በሌላ በኩል ከፏፏቴዉ ሥር 25 ሜትር ቁመት እና 66 ሜትር ርዝመት ያለዉ ዋሻ ይገኛል። ዋሻዉም “የእግዜር ድልድይ” በመባል ይጠራል። “ለምን ይህ ስያሜ ተቸረው?” ስንል በባሶሊበን ወረዳ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አንድ ባለሙያ ጠየቅን፡፡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ባለሙያው “ዋሻዉ የእግዜር ድልድይ ተብሎ የተጠራው በክረምት ወቅት የየዳና እና የበረደና ወንዝ ጢም ብለው ስለሚሞሉ ኅብረተሰቡ የሚሻገረው በዋሻው በኩል ስለኾነ ነው” ብለዋል።

ባለሙያው አክለውም ፏፏቴውን ከሩቅ ሲመለከቱት ዓይን ያጥበረብራል። በትኩረት ሲያዩትም ውኃው እንደ መልካም እስክስታ ወራጅ ሰው ይውረገረጋል። በመኾኑም ቀደምት የአካባቢው ማኅበረሰብ የውኃውን እንቅስቃሴ ተመልክተው “ውርግርግ” የሚል ስያሜ ሰጡት አሉን። የውርግርግ ፏፏቴ የሚገኝበት አካባቢ በደን የተሸፈነ በመኾኑ ለአዕምሮ እርካታን ለልብ ፍስሀን በጠቅላላው ለመንፈስ ሐሴትን ያላብሳል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ የፏፏቴው ዙሪያ መለስ በደን በመሸፈኑ የአካባቢው አየር ልዩ ነው። የመልክ ዓምድሩን ልምላሜ አንድ ጊዜ ለተመለከተ ጎብኝ “አትሂዱብኝ” ያስብላል ባይ ናቸው ባለሙያው። የአካባቢው ማኅበረሰብ በተለይ ቅዳሜ እና እሑድ በሳምንቱ ቀናት በሥራ የደከመ አዕምሮውን የሚያዝናናው ወደ ፏፏቴው ጎራ በማለት እንደኾነ ባለሙያው ነግረውናል።

ፏፏቴው ዙሪያውን በጠንበለል፣ ሽነት፣ ብሳና፣ ዋንዛ፣ ናጫ፣ እና ሌሎችም ሀገር በቀል ዛፎች የተሸፈነነው። ስለኾነም አካባቢው ለንብ አናቢዎች የተመቼ ነው። የተለያዩ የዱር አራዊት እና እንስሳት እንዲሁም አዕዋፍት የውርግርግ ዋሻ ወይም የእዜር ድልድይ ‘በመኖሪያነት’ ከትመውበታል።

መንግሥት የውርግርግ ፏፏቴን በተለያዬ ጊዜ ለማልማት መንቀሳቀሱን ባለሙያው አስታውሰዋል። ታዲያ ከመንግሥት ጎን ለጎንም ኅብረተሰቡ ይህን አንጡራ የሀገር ሀብት እየጠበቀ፣ እያለማ አንድም ሊዝናናበት እና ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እያስተዋወቀ የገቢ ምንጭ ሊያደርገው ይገባል በማለት አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here