በኢትዮጵያ ብቻ የምትገኘው ብርቅየዋ ሶረኔ

0
389

ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሶረኔ ወፍ በኢትዮጵያ ብቻ የምትገኘው ብርቅየዋ ወፍ ናት። ላባዋ በጥቁር እና ነጭ ጠቃጠቆ የተዋበ ነው። የዐይኖቿ ሽፋሽፍት ቀያይ ኾኖ ምንቃሯ ጥቁር እና ቀይ በመኾኑ ዐይነ ገብ ናት ፡፡ የእግር ቅልጥሞቿ እንሶስላ የሞቁ ይመስላሉ። ብርቅየዋ ሶረኔ ወፍ እንቁላል በመጣል ነው ዘሯን የምትተካው። በአንድ ዓመት በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ከአራት እስከ ሰባት እንቁላሎችን ጥላ በመታቀፍ ትፈጠፍጣለች።

ተባዕቱ ሶረኔ ብዙ ጊዜውን ከከእንስቷ ጋር አያሳልፍም። ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱትም ፆታቸውን ታሳቢ አድርገው ነው። ይች በኢትዮጵያ ብቻ የምትገኘው አንጡራ ሀብት (ሶረኔ) ለመኖሪያነት ተራራማ እና ገደላማ አካባቢ ኾኖ በደን የተሸፈነን ሥፍራ ትመርጣለች። ወፏ በሰዓት 30 ኪሎ ሜትር መብረር ትችላለች። ይች ብርቅዬ የወፍ ዓይነት በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ትገኛለች።

ሶረኔ ወፍ ከምትገኝባቸው ቦታዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙ ታሪካዊ የመስህብ ሥፍራዎች አንዱ የአቦ ዋሻ ነው። ይህ ዋሻ ከደብረ ብርሃን ከተማ 42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የአንኮበር ወረዳ መሐል ወንዝ ቀበሌ ውስጥ ይገኛል። ወደ ዋሻው ለመሄድ ከአንኮበር ወረዳ ርእሰ ከተማ ጎርቤላ በደብረ ብርሃን መስመር እስከ ጠምሴ ድረስ በመኪና አምስት ኪሎ ሜትር ድረስ ከተጓዙ በኋላም ጥቂት በእግር እንደሄዱ ጥቅጥቅ ያለ ደን ያገኛሉ፡፡

ደኑ ውስጥ አዕዋፋት ኅብረ ዝማሬ የሚያሰሙበት ነው። ወደ ውስጥ ሲዘልቁም የአቦ ዋሻን ያገኙታል፡፡ በአንኮበር ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የመስህብ እና ቅርስ ጥበቃ ባለሙያ አቶ የኋላ ዮሃንስ አቦ ዋሻ ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነ ነው፡፡ በውስጡም እንደ ዝግባ፣ ጽድ እና ወይራ የመሳሰሉት ይገኙበታል። በዚህ ደናማ ዋሻ ውስጥ ብርቅየዋ የሶረኔ ወፍ ትገኝበታለች።

በዚህ ዋሻ ከሶረኔ በተጨማሪ ዋኔ፣ ጭልፊት አሞራም ከትመውበታል ሲሉ አቶ የኋላ ገልጸዋል። የአቦ ዋሻን እንደ አሁኑ የጸጥታ ስጋት ባልነበረበት ጊዜ በርካታ ሰዎች ይጎበኙት ነበርም ብለዋል። ባለሙያ አክለው እንዳሉት ሶረኔዎች የሚያሰሙት ኅብረ ዝማሬ የሰውን ስሜት የመሳብ ኃይሉ ከፍተኛ ነው።

ብርቅየዋ ሶረኔ በደቡብ ወሎ ዞን የጃማ ወረዳም በብዛት ትገኛለች። ከወረዳው ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ባገኘነው መረጃ መንደቦ፣ ይርባ እና በቶ በሚባሉ ውኃማ አካባቢዎች ሶረኔ በብዛት ትገኛለች። ይህች ብርቅዬ ወፍ ትኖርበት የነበረዉ ደን በአንድ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ በመመናመኑ ቁጥሯ ቀንሶ ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲኽ ግን እየተሠሩ ባሉ የተራራ ልማቶች ምክንያት የተመናመነዉ የተፈጥሮ ደን መሻሻል በማሳየቱ የሶረኔ ወፍ ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here