ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ሙዚየም በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ነበር፡፡ ይህን ሙዚየም ወደነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በቅርሱ ላይ የሚካሄደው ጥገና በከፍተኛ ጥንቃቄ ነባር ይዞታውን ሳይቀይር እንዲካሄድ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው፡፡
በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ባለሙያ ጋሻየ መለሰ እንደነገሩን ሙዚየሙ 25 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጭ ጥገና እየተደረገለት ነው፡፡ ባለሙያው ሙዚየሙን በማደስ እና ከነበረበት የቀድሞ ይዞታ በተሻለ ደረጃ በማሻሻል ወደ ሥራ ለማስገባት ዲዛይን ሢሠራ ቆይቶ ከወር በፊት የተጀመረው እድሳት በፍጥነት እየተከናወነ ነው። እድሳቱም 37 በመቶ መድረሱን ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ድርጅት የቅርስ ጥገናውን እንዲያከናውን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ነው አቶ ጋሻየ ለአሚኮ የተናገሩት፡፡ በሙዚየሙ ውስጥ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የተሠበሩትን የመጠገን፣ የተዘረፉትን በማስመለስ በተሻለ አግባብ ቅርሱን ለማደራጀት ቢሮው ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን የጥገናው አባል ኾነው በከፍተኛ ጥንቃቄ ጥገናው እየተካሄደ ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) የደሴ ሙዚየም ከጥገና ባለፈ ሙሉ ግቢውን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ቦታ ለማድረግ የዲዛይን ሥራ እንደተሠራለት ተናግረዋል፡፡
ይህን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ የደሴ ሕዝብ፣ የከተማ አሥተዳደሩ እና የክልሉ መንግሥት በጋራ እንደሚሠሩም ነው የገለጹት። ዶክተር አየለ በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት እየተገነባ ያለው የሎጎ ሃይቅ የቱሪስት መዳረሻ ይበልጥ ጎብኚዎችን መሳብ የሚችለው በዙሪያው ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻዎች ሲኖሩ እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡ የደሴ ሙዚየምን፣ መርሆ ግቢን፣ አይጠየፍን እና ጦሳ ተራራን በማልማት የቱሪስቶችን ቆይታ ማራዘም ይገባልም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!