“አምባ ጽጌ” በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ነው የሚገኘው። ይህ አስደናቂ አምባ አስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን በተፈጥሮ ከታደሉ ቦታዎች ውስጥ ተጠቃሽ ነው።
አምባ ጽጌ ውበትን ከመንፈሳዊነት አጣምሮ የያዘ ነው። ማራኪ መልክዓ ምድር ሲኖረው የአምባ ጽጌ ገዳምም በዚሁ አለ። ቦታው ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይኾን የጥንተ ፖለቲካዊ ታሪክም አለው። በኢትዮጵያ የነገሥታት የሥልጣን ሽግግር ታሪክ ሥልጣን የያዘው አካል ለዙፋኑ የሚያሰጋውን ሰው ወደተመረጠ አምባ አውጥቶ በማስቀመጥ ከስጋት ነጻ ይኾን ነበር። ከገናናው የዛግዌ ስርዎ መንግሥት መዳከም በኋላ በአባቶቻቸው አልጋ የቀደመውን ሰፊ የዋግ አካባቢ በራስ ገዝነት ሲያሥተዳድሩ የነበሩ ዋግሹሞች ለወኅኒነት እንደተጠቀሙት ታሪክ ያመለክታል።
ዋግሹም ተፈሪ ወሰን ክንፉ በአምባ ጽጌ ወኅኒ ከነበሩ ዋግሹሞች መካከል አንዱ ናቸው።
ዋግሹም ተፈሪ በአምባ ጽጌ በእስር ላይ እያሉ የቋጠሩት እንደኾነ የሚነገር ስንኝም አሁን ድረስ ይነገራል፦
እናት የለኝ ደሃ ፡ አባት የለኝ ደሃ፣
እኔን ያሳደገኝ ፡ ያምባ-ጽጌ ውኃ። የሚል ነው።
ይህ ስንኝ ወደ አምባው ለግዞት የሚወጡ የንግሥና ዘር ሀረግ ያላቸው ሰዎችን ኑሮ የሚያመላክት ነው። ስንኙ የአምባውን የቀደመ አገልግሎት ለመጠቆም ጭምር ያግዛል።
የአምባ ጽጌ ተራራ አምባ-ጽጌ የሚለውን ስያሜ የያዘው የማኅሌተ-ጽጌ ደራሲ በኾኑት አባ ጽጌ ድንግል አማካኝነት እንደኾነ ይነገራል። አባ ጽጌ እንደ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እና በ14ኛው ክፍለ ዘመን ሰዓታትን እንደደረሰው አባ ጊዮርጊስ ሁሉ ማኅሌተ ጽጌ የተሰኘ መዝሙራዊ መልክ እና ለዛ ያለውን ወደ 150 የሚጠጋ እንዲሁም በብዛት 5 ስንኞች ያሉትን ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ያበረከቱ ናቸው፡፡ አባ ጽጌ ይህን ድርሰት ለሀገራቸው ያበረከቱት በዚሁ አምባ ላይ ተቀምጠው እንደኾነ ይታመናል።
በአምባው ላይ በርካታ ሃይማኖታዊ ቅርሶች አሉ። አባ ጽጌ በዘመናቸው እንደተገለገሉበት የሚታመነው በዓይነቱ ለየት ያለ እና የግላቸው “በትረ መስቀል” አንዱ ነው። እንዲሁም የተለያዩ ጥንታዊነትን የተላበሱ መስቀሎች፣ የድንጋይ ላይ ስዕሎች፣ የተፈለፈሉ የውኃ ማቆሪያ ጉድጓዶች እና ገንዳዎች፣ በርካታ ወፍጮዎችና ስብርባሪ ቁሳቁሶች፣ ለገበጣ ጨዋታ እና ለተለያዩ ጉዳዮች ያገለገሉ ቅርጾች እንዲሁም ጉድጓዶችም በአምባው የሚገኙ ቅርሶች ናቸው።
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ እንደሚያመለክተው ይህን ድንቅ ተፈጥሯዊ ውበትን ከመንፈሳዊነት፣ እንዲሁም የሀገሪቱን የጥንት ፖለቲካዊ ታሪክ ሰንዶ የያዘ ቦታ በሚገባው ልክ እየለማ እና እየተጎበኘ አይደለም። ቦታው በአቅሙ ልክ የቱሪዝም ሃብት እንዲያመነጭ በአግባቡ መልማት እና ለጎብኝዎች ምቹ መኾን እንዳለበትም ተጠቁሟል።
በአሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!