“የዘንድሮውን የልደት በዓል በላሊበላ ከእስካሁኑ በተለየ መልኩ በልዩ ድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው” የላሊበላ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጀ

0
242

የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ታሕሣስ 29 በኢትዮጵያ በልዩ ሁኔታ በዳግማዊት ኢየሩሳሌም ደብረ ሮሃ ላሊበላ በርካታ የዕምነቱ ተከታዮችና የውጭ ሀገር ዜጎች በተገኙበት በድምቀት የሚከበር ልዩ በዓል ነው፡፡

በምስጋና የሚከበረውን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሄም የተወለደበትና የቅዱስ ላሊበላን ልደት ኢትዮጵያውያን በታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ተገኝተው ያከብሩ ዘንድ ላሊበላ እንደተለመደው እንግዶቿን በክብር ጠርታለች፡፡

የልደት በዓል በላሊበላ የዕምነቱ ተከታዮች ፅድቅን የሚያገኙበት፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ልደትን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን እግር አጥቦ፣ የራበውን አብልቶ፣ የተጠማውን አጠጥቶ፣ የሚያርፍበትን ቦታ አመቻችቶ የሚያስተናግድበት፣ በረከትን፣ የእርስ በርስ ግንኙነትን የሚያጎለብትበትና ማኅበራዊ ቁርኝትን የሚያገኝበት ልዩ በዓል ነው።

የ2016 የልደት በዓልን በድምቀት ለማክበር ከተማ አሥተዳደሩ ልዩ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ወንድምነው ወዳጀ ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮው የልደት በዓል ከእስካሁኑ በተለየ መልኩ በልዩ ሁኔታ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባው፤ ከወጣቶች፣ ከዕምነት አባቶች፣ ከዕድር መሪዎችና ከመንግሥት አካላት የተውጣጣ አንድ አብይ ኮሚቴ በስሩ 6 ንኡሳን ኮሚቴዎች ያሉት አደረጃጀት ተዋቅሮ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

በዓሉን በድምቀት ማክበር ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባለፈ አከባባው የቱሪስት ቀዳሚ መዳረሻ እንደመሆኑ ከ2012 ጀምሮ በተከሰተው ኮሮናና በጦርነት ምክንያት የቱሪስት ፍሠት የቀዘቀዘ በመሆኑ ዘርፉን ለማጠናከር በዓሉን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

የዕምነቱ ተከታዮች፣ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገር ዜጎች ሕዝቡ በተለመደው የእንግዳ አቀባበል ባሕሉ በልዩ ሁኔታ አስተናግዶ በሰላም የሚመልስ በመሆኑ ገናን በላሊበላ እንዲያከብሩ ሲሉ ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዘገባው የላሊበላ ከተማ ኮሙኒኬሽን ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here