የዘመን ተሻጋሪ ቅርሶች ባለቤት መርጡለ ማርያም!

0
527

ባሕር ዳር: ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን በእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ የምትገኘው መርጡለ ማርያም ገዳም ከ2000 ዓ.ዓ ጀምሮ የጊዮንን ወንዝ ተከትለው የመጡ የነገደ ካምና የኩሽ ዘሮችን የተቀበለች ቦታ ናት ይሏታል፡፡ይህች ጥንታዊ ገዳም ከአዲስ አበባ ሰሜናዊ አቅጣጫ በ367 ኪሎ ሜትር፣ ከባሕር ዳር 181 ኪሎ ሜትር፣ ከደብረ ማርቆስ 187 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ጥንታዊ ገዳም ናት፡፡

ከዓባይ ወንዝ በቅርብ እርቀት በሚገኝ ኮረብታ ላይ የምትገኘው መርጡለ ማርያም የወይና ደጋ የአየር ንብረት ባለቤትም ናት፡፡ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው ገዳሟ አሁን የያዘችውን መጠሪያ ስም ከመያዝዋ በፊት በተለያዩ ዘመናት በመጀመሪያ ሀገረ ሰላም፣ ቀጥሎ ሀገረ እግዚአብሔር፣ ለሦስተኛ ጊዜ ጽርሐ አርያም በመጨረሻም አሁን የምትጠራበትን መርጡለ ማርያም የሚል ስያሜ አግኝታለች፡፡

ይህች ታላቅ እና ጥንታዊት ገዳም የተመሠረተችው ከእስራኤሉ ንጉስ ሰለሞን እና ከኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ (ማክዳ) የተወለደው ቀዳማዊ ሚኒሊክ ይዟቸው በመጡ የኦሪት ካህናት በ4ሺህ 500 ዓ.ዓ ነው፡፡ በገዳሟ በ333 ዓ.ም አካባቢ በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት እንደተሠራ የሚታመን በልዩ ልዩ ጌጣ ጌጦች በተዋቡ ድንጋዮች የተሠራ የሕንጻ ፍርስራሽ ይገኛል፡፡

የሕንጻው አስደናቂነት የሚጀምረው ከበሩ አሠራር ሲኾን የግማሽ ክብ ቅርጽ ያለው በአበባ እና ሐረግ የተጌጠ ሰፊ የበር አምድ፣ መስኮቶች፣ ከሕንጻው አናት ላይ የሚገኙ ከድንጋይ የተቀረጹ ስዕለ ጽላት፣ ስዕለ ኪሩብ እና ልዩ ልዩ ቅርጻ ቅርጾች በሕንጻው አብዛኛው ክፍል ከውድመት ተርፈው ከነውበታቸው ዛሬም ድረስ ይታያሉ፡፡

አብርሃ ወአጽብሃ የሕንጻው አምዶችን እና ዓረፍተ መቅደሱን እጅግ በተዋበ የድንጋይ ሐረግ ቅርጽ አስጊጠው በወርቅ እና በዕንቁ አስለብጠውት እንደነበርም ይነገራል፡፡ ይህ በልዩ ቅርጽ ተውቦ የተሠራ ባለ 12 ቤተ መቅደስ በወቅቱ በነበረ ችግር እንደወደመ ይነገራል፡፡ የፈረሰው ሕንጻ እንደገና ለመታደስ ዕድል ያገኘው በእደ አምደ ማርያም ዘመነ መንግሥት በ1460 ዓ.ም አካባቢ በንግሥት እሌኒ አማካኝነት ነበር፡፡

በአሁን ሰዓት የሕንጻው አብዛኛው ክፍል ፈራርሶ በነበረበት ባይገኝም ለታሪክ ነጋሪነት ከጉዳት ተርፈው የሚገኙ ግድግዳዎች፣ በሮች፣ መስኮቶች እና አምዶች እጹብ ድንቅ የነበረውን የሕንጻውን የአሠራር ጥበብ በዓይነ ህሊና ለማሰብ እና ለመደመም ያስችላል፡፡

መርጡለ ማርያም ከረጅም የምሥረታ ዘመኗ አንጻር እና ከነበራት ከፍተኛ ሀገራዊ ከፍታ የተነሳ የአያሌ ውድ ቅርሶች ባለቤትም ናት፡፡ እነዚህ ውድ ቅርሶች ገዳሟን በአጋጠሟት የጥፋት ዘመኖች ሁሉ በአባቶች ጥበብ ከጥፋት ተሰውረው ከትውልድ ትውልድ በመተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

በገዳሟ ከሚገኙ ቅርሶች መካከል ጥቂቶቹ በ445 ዓ.ም የተጻፈ ግዕዝን በግዕዝ የሚተረጉም አርባዕቱ ወንጌል፣ የአጼ በእደ ማርያም ራስ ቁር እና የወርቅ ለምድ፣ የንግሥት እሌኒ የክብር ካባ እና የብር ዋንጫ፣ የብር እና የወርቅ መስቀሎች፣ የወርቅ አክሊሎች፣ የወርቅ ከበሮ፣ የአጼ ገላውዲዮስ ዳዊት እና ካባ፣ የብራና መጻሕፍት እና መሰል ቅርሶች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here