የሙሉዓለም የባሕል ማዕከል የኪነ ጥበብ ልዑክ ኢትዮጵያን በመወከል ወደ ሩሲያ ካዛን ከተማ አቀና።

0
128

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የልዑክ ቡድኑ በሩሲያ ካዛን ከተማ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የባሕልና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ ለመሳተፍ ነው ወደ ቦታው ያቀናው። በዚህ ፌስቲቫል ላይ 12 የሚደርሱ የባሕል ማዕከሉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ።

የሙሉዓለም የባሕል ማዕከል ዋና ዳይሬተር ገብረ ማርያም ይርጋ ልዑኩ ከኅዳር 16 እስከ 24/2017 ዓ.ም በሚካሄደው ፌስቲቫል የኢትዮጵያን ባሕልና የኪነ ጥበብና እሴቶች የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል ብለዋል። አቶ ገብረማርያም እንዳሉት የባሕል ማዕከሉ ላለፉት 25 ዓመታት የክልሉን ታሪክ እና ባሕል በተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች በማዘጋጀትና በማቅረብ የሕዝቡን ቱባ ባሕልና ትውፊት ለሌሎች ሲያስተዋውቅ ቆይቷል።

ባሕል ማዕከሉ እሴቶችን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እያዝናኑ የሚያስተምሩ የጥበብ ሥራዎችን በማቅረብ፣ ፍልስፍናዉን፣ እሴቱን፣ ወጉን እና ሥነ ልቦናዉን እየገለጠ፣ እያስተማረ፣ እያሰረጸና እያስተዋወቀ ነውም ሲሉ አብራርተዋል። ሙሉዓለም የባሕል ማዕከል በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሕዝብ እና ሀገርን በሚመለከቱ ጉዳዮች ሁሉ ግንባር ቀደም ተሰላፊ ሆኖ እየሠራ የሚገኝ ማዕከል ስለመኾኑም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ “በሩሲያ ካዛን ዓለም አቀፍ መድረክ የሀገራችንን ባሕልና ኪነጥበብ ከማስተዋወቅ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ከማድረግ ባሻገር ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከሚመጡ የዘርፉ እውቅ ባለሙያዎች ጋር የልምድ ልውውጥ እናደርግበታለን ብለዋል። መድረኩ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገሮች ጋር ግንኙነት በማድረግ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ እንደ ሀገር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም አብራርተዋል።

በሩሲያ ካዛን ከተማ እየተካሄደ በሚገኘዉ የባሕል ፌስቲቫል የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አመራሮች ኢትዮጵያን በመወከል ቀድመዉ መግባታቸው ይታወሳል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here