ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በከተማዋ እና አካባቢው ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ማዳከሙን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ዮናስ ይትባረክ ገልጸዋል።
በቱሪዝሙ መቀዛቀዝ በዘርፉ በቀጥታ ተጠቃሚ የኾኑ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እና አስጎብኝዎች ይበልጥ ተጎጅ ቢኾኑም በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የኾኑ አካላት ጭምር ምጣኔ ሃብታዊ ኪሳራ እንዳጋጠማቸው ገልጸዋል፡፡
የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ከጥር/2016 ዓ.ም መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ የተለያዩ ሁነቶችን ለማዘጋጀት የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ኀላፊው እንዳሉት ከጥር 5/2016 ዓ.ም እስከ ጥር 10/2016 ዓ.ም የባሕል ሳምንት ይካሔዳል፡፡
በዝግጅቱ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች የተወከሉ የባሕል ቡድኖች የጎዳና ላይ ትርኢት ያሳያሉ፡፡ ጥር 6/2016 ዓ.ም የአጼ ቴዎድሮስ የልደት በዓል እንደሚከበር ነው የነገሩን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ይካሄዳሉ፡፡ በከተማ አሥተዳደሩ የተሠሩ መሠረተ ልማቶች ጉብኝት እና የኢንቨስትመንት አማራጮች ፎረም እንደሚካሄድም ገልጸዋል፡፡
የጥምቀት በዓልን በድሞቀት ለማክበርም ባሕረ ጥምቀቱን እና ታዳሚዎች የሚያርፉባቸውን ቦታዎች የማደስ እና የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ለአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እና አስጎብኝዎች ሥልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡ በቱሪዝሙ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመመለስ ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጠይቀዋል፡።
➽ በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያው አምስት ወራት በከተማዋ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከጎበኙ 30 ሺህ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች 463 ሺህ ብር ገቢ ተገኝቶ ነበር።
➽ በ2016 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ይጎበኛሉ ተብሎ ከታቀደው የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች 38 በመቶ ብቻ ናቸው የጎበኙት፡፡
ከ696 የውጭ ጎብኝዎች 139 ሺህ 475 ብር ገቢ እንደተገኘም ተገልጿል። ይህም በአብዛኛው በሱዳን በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ወደ ከተማዋ የመጡ ሱዳናውያን ጎብኝዎች እንደኾኑ የቢሮው መረጃ ያሳያል፡።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!