ባሕር ዳር: ጥር 07/2017 ዓ.ም(አሚኮ) ጠቢባን ነገሥታት አስውበዋታል፣ በጠቢባን እጆቻቸው አስጊጠዋታል፣ በጠቢብ አዕምሯቸው አልቀዋታል። በታሪክ አንግሠዋታል። በጠቢባን ነገሥታት አብዝታ የተወደደች፣ ከፍ ብላም የተከበረች አድርገዋታል። የተዋቡ አብያተክርስቲያናትን፣ የረቀቁ አብያተ መንግሥታትን አንጸውባታል፣ ሕግ እና ሥርዓትን ሠርተውባታል። ትውልድ ሁሉ የሚጓዝበትን መልካሙን ጎዳና ቀይሰውባታል። የሀገርን አንድነት ጠብቀውባታል።
ጠቢባን ሊቃውንት አሳምረዋታል፣ ጥበብን እንደ ወራጅ ውኃ አፍስሰውባታል፣ ለተጠማ ትውልድ ሁሉ አጠጥተውባታል፣ ለትናንቱ፣ ለዛሬው እና ለነገው ትውልድ የሚኾን መልካም ነገር አኑረውባታል። ሃይማኖትን አጽንተውባታል። የከበደውን እያቀለሉ፣ የራቀውን እያቀረቡ ምስጢር ፈትተውባታል። ሌሎች ባልሰለጠኑበት፣ በጨለማ በርኖስ ውስጥ በነበሩበት በዚያ ዘመን እነርሱ ዕውቀትን አፍስሰውባታል፣ በቤተ መንግሥቱ እና በቤተ ክህነቱ ትምህርትን አስፋፍተውባታል።
በዚያች ምድር ትውልድ የሚኮራባቸው፣ ሀገር የምትከበርባቸው፣ በዓለሙ ፊት ሁሉ ከፍ ብላ የምትታይባቸው፣ ቀደምት ሥርዓተ መንግሥት፣ ቀደምት ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንዳላት የምታሳይባቸው፣ የሥልጣኔዋን ወሰን የምትነግርባቸው፣ የታላቅነቷን ልክ የምትገልጽባቸው፣ የከፍታዋን መጠን የምታሳውቅባቸው የጥበብ አሻራዎች ሞልተዋል።
የሀገር አንድነት ይሰበክባታል፣ ለሀገር ከፍታ ይመከርባታል፣ ለሥልጣኔ ይመክሩባታል ይዘክሩባታል ጎንደር። የመናገሻዋ ከተማ እየተባለች ትጠራለች፣ የአፍሪካ መናገሻ እየተባለች ትወደሳለች። ዙፋን ለዓመታት ረግቶባታል፣ የኢትዮጵያ የአንድነት ውል ተጠብቆባታል፣ የሀገር ዳር ድንበር ጸንቶባታል። ሥልጣኔ እንደ ማለዳ ጮራ ፈክቶባታል። እንደ ቀትር ፀሐይ ከፍ ብሎ አብርቶባታል። እንደ ፀደይ አበባ አጊጦባታል። እንደ ገዘፈ ተራራ ከፍ ብሎ ታይቶባታል።
ዕውቀት እንደ ጥልቅ ውቅያኖስ ጠልቆባታል። ባሕር የሚሰነጥቁ፣ የብስ የሚያቋርጡ ነጋዴዎች ግመሎቻቸውን የሚያሳርፉባት፣ የጫኑትን ወርቅ እና አልማዝ፣ የከበረውን ማዕድን ሁሉ የሚያራግፉባት፣ በሰላም እና በተድላ የሚኖሩባት፣ ቤታችን፣ ማረፊያችን፣ የጭንቅ ዘመን ማለፊያችን የሚሏት ናት ጎንደር።
በመናገሻዋ ከተማ በጎንደር ዓይን ሁሉ የሚሳሳላቸው አብያተክርስቲያናት፣ ልብ ሁሉ የሚደነግጥላቸው አብያተ መንግሥታት በክብር ይኖሩባታል። በታሪክ ሰገነት ላይ ከፍ ብለው ይታዩባታል። ከበዙት አብያተክርስቲያናት መካከል ደግሞ ታላቁ ንጉሥ አድያም ሰገድ ኢያሱ አስውበው ያሠሩት፣ ዘውዳቸውን ጥለው ያገለገሉት፣ ካባቸውን አውልቀው እጅ የነሱለት፣ ስማቸውን ከእርሱ ጋር እንዳይለያይ አድርገው በታሪክ ማሕተም ያተሙበት ጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴ አንዱ ነው።
የጠቢባን አሻራ፣ የመናገሻዋ ሙሽራ የኾነው ታላቁ ቤተክርስቲያን በታየ ቁጥር እጹብ ድንቅ የሚባልለት፣ ለማድነቂያ አንደበት የሚጠፋለት ያማረ እና የተዋበ ነው። በደብረ ብርሃን ሥላሴ በእያንዳንዱ ኪነ ሕንጻ፣ በእያንዳንዱ ሥራ ሁሉ ታሪክ ይነገርበታል፣ ትርጉም ይተረጎምበታል፣ ምስጢር ይመሰጤርበታል። ያለ ምክንያት የተሠራ፣ ያለ ትርጉም የቆመ ምንም ነገር አይገኝምና። ሁሉም በምክንያትነት እና በምልክት ተሠራ እንጂ። ይህ ቤተክርስቲያን የጎንደር ታላቅነት እና የጥበብ ምንጭነት ከሚገለጥባቸው የበዙ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ቅርሶች መካከል አንደኛው ነው።
አሰግድ ተሰፋዬ ጎንደር የአፍሪካ መናገሻ በተሰኘው መጽሐፋቸው ስለ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሲጽፉ ከአብያተ መንግሥታቱ በቅርብ ርቀት በሚገኝ አምባ ላይ የጎንደሩ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያን ይገኛል። አድያም ሰገድ ኢያሱ ከሸዋ ደብረ ብርሃን አዲስ ላሠሩት ቤተክርስቲያን የሥላሴን ታቦት አስቀርጸው ማምጣቸውም ይነገራል። ታቦቱ በመጣበት ዘመንም የሸዋ መርድ አዝማቾች ደብረ ብርሃን የሚለውን ስያሜ እንደጨመሩላቸው ይነገራል። በዚህም ምክንያት ደብረ ብርሃን ሥላሴ እየተባለ ተጠራ ይላሉ።
ታምራት ወርቁ የመማጸኛ ከተማ በተሰኘው መጽሐፋቸው ታላቁ ኢያሱ ባሳነጹት ቤተክርስቲያን ታቦተ ጽዮንን ማስገባት አስበው እንደነበር ጽፈዋል። ነገር ግን ሁሉም በእግዚአብሔር ፈቃድ ይፈጸማልና ታቦተ ጽዮን ሳትኾን ሥላሴ ገባበት። ታቦቱም ስያሜውም ከሸዋ ደብረ ብርሃን እንደመጣም መዝግበዋል። ነገር ግን ደብረ ብርሃን ለተባለበት ስያሜ ሁለት ሺህ መክሊት ወርቅ ከፍለዋል በማለት ጽፈዋል። ስለ ምን ደብረ ብርሃን የሚለውን ስያሜ መረጡ ሲባል ቦታው ብርሃን የወረደበት በመኾኑ በሁኔታው ተማርከው ነው ይባላል።
ተክለጻድቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ በተሰኘው መጽሐፋቸው ንጉሡ አድያም ሰገድ ኢያሱ ያልገበረውን አስገብረው ሀገርም አይተው ከመናገሻዋ ከተማ ጎንደር ሲገቡ የደብረ ብርሃን ሥላሴ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ አልቆ ነበር፡፡ ወደ አዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ታቦቱ በሚገባ ጊዜም ታቦቱን ከአባ ሲኖዳ በኋላ የተሾሙት ጳጳሱ አቡነ ማርቆስ ዕጬጌው ጸጋ ክርስቶስ ከቀሳውስቱ ጋር ይዘው ፊት ለፊት ሲሄዱ ንጉሡ ጎቤን በሚባለው ፈረሳቸው ተቀምጠው በመኳንቶቻቸው ታጅበው ታቦቱን ከኋላው ይከተሉ ነበር፡፡
በኋላም ታቦቱ በቤተክርስቲያን ደጃፍ በደረሰ ጊዜ ንጉሡ ታቦቱን ከቄሱ ተቀብለው (ገና በጳጳሱ አልተባረከም ነበርና) በራሳቸው ተሸክመው ቅድስት ድረስ አስገቡ፡፡ ከዚያ ቄሱ ተቀብሎ ከቅድስት ወደ መቅደስ ካስገባው በኋላ በጳጳሱ ተባርኮ ቅዳሴ ቤቱ ከብሮ የታቦቱ አገባብ በታላቅ በዓል ተከበረ፡፡ በዚህም ቀን ለካህናት እና ለወታደር፣ ለመኳንንት እና ለሊቃውንት ትልቅ ግብር በደብረ ብርሃን አደረጉ፡፡ አዛዥ ሐዋርያ ክርስቶስም ለንጉሡ መወድስ ተቀኙላቸው፡፡ ሌሎች ሊቃውንትም ለንጉሡ ተቀኙላቸው ብለው ጽፈዋል።
በዚያ ቀን ስለ ንጉሡ ከተባሉት መካከል “ዮሐንስ በማጥመቁ ምስክርነት ሳለ የሥላሴን ሦስትነት የዮርዳኖስ ባሕር እንደቻለ፤ ኢያሱ የሠራውን የመቅደሱን ደብር ሦስትነት ያለበት የኪሩብን ዙፋንነት አደረገ” የሚለው አንደኛው መኾኑም ተጽፏል። በዚያ ዘመን የነበሩ ባለቅኔዎች የተቀኙት ቅኔ ዛሬ ድረስ ይነበባል፤ ዛሬም ድረስ ለአድያም ሰገድ ኢያሱ ይገጠማል፡፡
“ወዴት ሄዶ ኖሯል ሰሞነኛው ቄሱ
ታቦት ተሸከመ ዘውዱን ትቶ ኢያሱ” እየተባለ። ንጉሥ ኢያሱ ከፈረስ ወርደው፣ ዘውዳቸውን ጥለው ታቦት ተሸክመው እስከ ቅድስት ድረስ ሄደዋል። ከእርሳቸው ንግሥና ይልቅ ለማያልፈው ለሰማዩ ንጉሥ ክብርን ሰጥተዋልና ተቀኙላቸው። አከበሯቸው። አባታቸው አጼ ዮሐንስ ካህን እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ነገር ግን ክህነታቸውን አልገለጡም ነበር ይባላል፡፡ በንግሥናው ውስጥ ክህነትን እና ደግነትን ይዘው የተወደደውን ሲያደርጉ እንደኖሩ ይነገራል። ልጃቸው ኢያሱ ግን ታቦት ተሸክመው ታይተዋልና እንዲህ ሲሉ ተቀኙላቸው፡፡
“የተሸሸገውን ያባቱን ቅስና
ገለጠው ኢያሱ ታቦት አነሳና፡፡
አየነው ኢያሱን ደብረ ብርሃን ቆሞ
ከኪሩቤል ጋራ ሦስቱን( ሥላሴን) ተሸክሞ
ሰውነቱን ትቶ መልአክ ኾነ ደግሞ፡፡
ሥላሴን ቢሸከም ኢያሱ ገነነ
ላራቱ ኪሩቤል አምስተኛ ኾነ” በማለት የጎንደር ሊቃውንት ታላቁን ንጉሥ አሞገሷቸው። ይህ ስለ እርሳቸው የተገጠመ ግጥም ዛሬም ድረስ ስለ ደብረ ብርሃን ሥላሴ በተነሳ ቁጥር ሳይነገር፣ ሳይዘከር አያልፍም። ተክለጻድቅ ሲጽፉ ታቦቱ ከገባ በኋላ የቤተክርስቲያኑ አገልጋዮች ቤተክርስቲያኑን ሞሉት፡፡ ንጉሡም ለአሠሩት ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ርስት እና ጉልት ተከሉለት፡፡ የቤተ ክርስቲያኑን አለቃም “ መልአከ ብርሃናት” የሚል ማዕረግ ተሰጣቸው ብለዋል። ታምራት ወርቁ ደግሞ መናኝ የነበሩት ቀውስጦስ የሚባሉት ሊቅ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተሾሙ፣ የደብሩ አለቃ የመጀመሪያ ስም ” ሊቀ ካህናት” እንደነበር፣ ወዲያም ተለውጦ ” መልአከ ብርሃን” እንደተባለ ጽፈዋል።
አሰግድ ተስፋዬ ስለ ደብረ ብርሃን ሲጽፉ የቤተክስቲያኑ ጉልላት በአድያም ሰገድ ኢያሱ በወርቅ የተሠራ ነበር ብለዋል። ያም ጉልላት እንደ ፀሐይ ያበራ ነበር ይባላል። አሁን ላይ ግን ሦስት የጎንደር መስቀሎች ይታዩበታል። እነዚህም መስቀሎች የተሰቀሉት በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ነው በማለት አስፍረዋል። የቤተክርስቲያኑ አሠራር መርከብ እንደሚመስልም ይነገራል።
ታምራት ወርቁም ስለ ቤተክርስቲያኑ አሠራር ሲጽፉ ” አጼ ኢያሱ የአድባራት ሁሉ ንግሥት በማለት ደብረ ብርሃን ሥላሴ ብለው የሰየሙትን ቤተክርስቲያን ለየት ባለ መልኩ አሳንጸው የወርቅ ጉልላት በላዩ ላይ አሠርተው ከወርቅም የተሠራ መስቀል እንዲኖረው አድርገው በቀን እንደ ፀሐይ፣ በሌሊት እንደ ጨረቃ ያንጸባርቅ ነበር። በማይነቅዝም እንጨት በአዋቂዎች እጅ አስጠርበው የታቦቱን መንበር አሠሩ። ይህ ቤተክርስቲያን ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላም በዙሪያው ልዩ ልዪ አትክልቶች እንዲተከሉ እና ዛፎች እንዲከቡት ስለ ተደረገ ዛሬም ታላላቅ ዛፎች አጥረውት ይገኛል” ብለዋል።
ቤተክስቲያኑ ጣሪያውን ደግፈው የሚይዙ 24 ምሰሶዎች አሉት። እነዚህም 24ቱን ካህናተ ሰማይ ይወክላሉ ይባላል። ቤተክርስቲያኑ ዙሪያ ምስጢር የሚነግሩ 12 ኪነ ሕንጻዎች አሉ። እነዚህም የእንቁላል ቅርጽ ያላቸው የእንቁላል ግንብ እየተባሉ ይጠራሉ። የቤተክርስቲያኑ ደጀ ሰላም በአንበሳ ቅርጽ እንደተሠራም ይነገራል።
ይህ ታላቅ ቤተክርስቲያን በውስጡ የኢትዮጵያውያንን ሊቃውንት የጥበብ ረቂቅነት በሚገልጽ እጅግ ባማሩ መንፈሳዊ ሥዕሎች የተዋበ ነው። ስዕሎቹ ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚያስተምሩ፣ በመጻሕፍ ያለውን በስዕል ያሳዩ፣ የቀደመውን ጥበብ እና ዕውቀት የሚገልጹ፣ የኢትዮጵያ ሊቃውንትን ታላቅነት የሚዘክሩ ናቸው። ለዘመናት እንደረቀቁ የዘለቁት ስዕሎች ዛሬም ድረስ እጹብ ድንቅ እየተባሉ ይኖራሉ።
የደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሥዕሉ አሣሣሉ ብቻ ሳይኾን የሚመስጠው የአቀማመጥ ሁኔታው ጭምር ነው። በአራቱም ንፍቅ ስለተሳሉት፣ በቤተክርስቲያኑ ጣሪያም ላይ ስለ ረቀቁት ስዕላት መግለጽ ከባድ ስለ ኾነ እንዲው እጹብ ድንቅ ብሎ ማለፍ ይቀላል ብለዋል ታምራት ወርቁ በመጽሐፋቸው።
ይህ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቤተክርስቲያን የጎንደር አድባራት በመሐዲስቶች ሲቃጠሉ ሳይቃጠል የተረፈ የጥንቱን ውበት እና ግርማ ይዞ እንዳለ ይነገራል። መሐዲስቶች የጎንደር አብያተ ክርስቲያናትን እያቃጠሉ ሲመጡ ከቤተክርስቲያኑ ቅጽር የወጣ የንብ መንጋ አላስቀርብ አላቸው። መሐዲሰቶችም መድፈር ተሳናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ድረስ በቤተክርስቲያኑ የቅጽር መዝጊያ በር ያለው እና የሳንቃው ሚካኤል እየተባለ የሚጣራው በቁጣ በመገለጡ መሐዲሰቶች ፈርተው ሸሹ ይባላል በማለት አሰግድ ጽፈዋል። የሳንቃው ሚካኤል ዛሬም ድረስ ጎብኚዎች ወደ ቤተክርስቲያኑ በሄዱ ቁጥር ታሪኩ ይነገራል።
ታምራት ወርቁ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ስለተረፈበት ታሪክ ሲጽፉ ደግሞ “ድርቡሾች ጎንደር ከተማዋን ሲያቃጥሉ ሕዝቡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በመሠብሠብ ጸሎተ ምሕላ ያደርግ ነበር። በዚህ ወቅትም ሰማዩ በጉምና በጭስ ይሸፈን ነበር። ቤተ ክርስቲያኑ እንዲጠፋ የፈለጉ ሰዎችም ደብረ ብርሃን ሥላሴ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ካልተቃጠለና ካልጠፋ ጎንደር እንዳልጠፋች ይቆጠራል እያሉ ለድርቡሾች መንገድ ይመሩ ነበር። ድርቡሾችም በሩን ለመሥበር የተቻላቸውን ያህል ቢያደርጉም ሳይኾንላቸው ይቀራል። እንጨት ሠብሥበው አቃጥለው ለመግባት ሲሞክሩ ከበሩ ላይ ያለው የሳንቃው ቅዱስ ሚካኤል ሰይፍ እየመዘዘ ታያቸው። በዚህም ምክንያት ትተው ሸሹ” ብለዋል።
ይህ ታላቅ ቤተክርስቲያን በጣልያን የወረራ ጊዜም ከመከራዎች የተሻገረ፣ ጥንታዊነትን፣ ከውበት እና ከረቂቅነት ጋር አጣምሮ የያዘ እንደኾነ ይነገርለታል። ጥንታዊው ደብረ ብርሃን ሥላሴ ከሕንጻ ቤተክስቲያኑ ማማር፣ ከተዋቡ ስዕሎች፣ በዙሪያው ካሉ ምስጢራዊ ኪነ ሕንጻዎች ባሻገር በውስጡ መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ቅርሶችን አቅፎ ይዟል። ጎንደርን የጎበኘ ሁሉ በቅጽሩ እየተመላለሰ ያየዋል። በጥንታዊነቱ፣ በክብሩ እና በረቂቅነቱ ይደነቃል፣ ይገረማል።
ደብረ ብርሃን ሥላሴ በጥር ሰባት ምዕምናን ይሰባሰቡበታል፡፡ ለጥምቀት በዓል ቀደም ብለው ጎንደር የገቡ ጎብኝዎች እና አማኞች ይከቡታል፡፡ ለጎንደር ውበት፣ ማንነት፣ ጌጥ እና ፈርጥ ነው፡፡ ጎንደር በጥር ከምትደምቅባቸው በዓላት መካከል አንደኛው የደብረ ብርሃን ሥላሴ ዓመታዊ ክብረ በዓል ነው፡፡
ሂዱና ተመልከቱት የትናንቱን ከእነ ውበቱ እንደያዘ ታገኙታላችሁ። የኢትዮጵያን ቀደምትነት፣ የኢትዮጵያን የሥልጣኔ መሪነት፣ የዘመን ጮራነት ትመሰክሩበታላችሁ። የኢትዮጵያን የኪነ ሕንጻ፣ የሥነ ሥዕል እና የሌሎች ዕውቀቶችን ታላቅነት ታዩበታላችሁ። ደብረ ብርሃን ሥላሴ የንጉሡ አሻራ፣ የዘመናት ሙሽራ ነው፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!