ታንኳውም ያው፣ ሐይቁም ያው!

0
117

ባሕር ዳር: ጥር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጥርን በባሕር ዳር በበርካታ ኹነቶች ታጅቦ በተደራጀ መልኩ እየተከበረ የባለዘንባባዋን ከተማ ቱሪስቶች እና ወዳጆች ቀልብ መሳብ ከጀመረ እነኾ ስምንት ዓመት ሞላው። ጥርን በባሕር ዳር በየዓመቱ ከገና ቀደም ብሎ እየተጀመረ ጥርን በሙሉ ከተማዋን ይሞሽራል።

በ2017 ጥርን በባሕር ዳር መርሐ ግብር ከተማዋ ከአሚኮ ጋር በመተባበር በገና ዋዜማ “እንቁ ምስጋና” ብላ ደግ የሠሩላትን ልጆቿን አመስግናለች። በልደት፣ በከተራ እና በጥምቀት በዓልም እንግዶቿን ከሩቅ ጠርታ በልዩ ድምቀት፣ በፍቅር እና በሰላም አስተናግዳለች። ባሕር ዳር ዓለም “የትምህርት ከተማ” ብሎ ዕውቅና የሰጣት ከተማ ናት። ይሄንን የሚያሳይ የመጽሐፍት ዐውደ ርዕይ ተዘጋጅቶ ታላላቅ ሰዎች ለወጣቶች ልምዳቸውን አጋርተዋል። ዓለም ለባሕር ዳር በሰጣት ክብር ልክ አንባቢ እና የበለጠ አዋቂ ትውልድ ይፈጠር ዘንድም ተመክሯል።

ጥር ከገባ ወዲህ ባሕር ዳር አልተኛችም። ወዲህ ለውበቷ የሚበጃትን የኮሪደር ልማት እያጧጧፈች ነው፤ ወዲያ ለእንግዶቿ ምቾት እና ሀሴት በማሰብ ወገቧን አስራ የተለያዩ ሁነቶችን እያሰናዳች ነው። ነገ ጥር 15/2017 ዓ.ም ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ የተደገሰው ሁነት ደግሞ ይለያል። የሐይቁን ባለሞገድ ውኃ የመሬት ያህል በሚደፍሩት ዋናተኞች የሚቀዘፉ ታንኳዎች እና ባለሞተር ጀልባዎች ሁሉም ተጠራርተው በታላቁ ጣና ሐይቅ ላይ ይገናኛሉ። ታንኳውም ያው፣ ሐይቁም ያው ነው። ቀዛፊዎች በተንጣለለው ሐይቅ ላይ ይፋለማሉ፤ የሐይቁን ሞገድ ነግሠውበት ቀድመው የደረሱ ይሸለማሉ።

ጀልባዎችም በታንኳዎች ዙሪያ በልዩ ሰልፍ ሐይቁን እየከፈሉ ልዩ ትርኢት ያሳያሉ። ታንኳ እና ጀልባዎች ነገ ታላቁን የጣና ሐይቅ በሞገድ ያስጨንቁታል! ሁነቱ ቀርበው ሊያዩት እንጅ “እንዲህ ነው” ብሎ ሊገልጡት የማይችሉት ውበት ነው ያለው።

ይህ ሁሉ ነገ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ይኾናል። የታንኳ ቀዘፋው፣ የጀልባ ትርኢቱ እና ሽርሽሩ የባለዘንባባዋ ከተማ ጌጥና ልዩ ድምቀት ሊኾን ሙሉ ዝግጅት ተደርጓል። የባሕር ዳር ወዳጆች ሁሉ በታላቁ ሐይቅ ዳርቻ አምሮ በተገነባው አረንጓዴ ሥፍራ ላይ ከትመው፣ አልያም በጀልባዎች ወደሐይቁ እየገቡ ሁነቱን እንዲታደሙ ከተማ አሥተዳደሩ የክብር ጥሪውን ለእንግዶቹ አስተላልፏል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here