‘’ የአገው ፈረሰኞች በዓል የጀግኖች አባቶቹን ታሪክ እየዘከረ እና ትውልድ እየቀረጸ ነው” አየለ አናውጤ (ዶ.ር)

0
128

ባሕር ዳር: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 85ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል “አርበኝነታችን ለአሁናዊ ሰላማችን” በሚል መሪ መልዕክት በእንጅባራ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው። በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ያለፉትን 85 ዓመታት የጀግኖች አባቶቹን ታሪክ እየዘከረ እና ትውልድ እየቀረጸ ያለ ነው ብለዋል።

ፈረስ የአገው ሕዝብ የክብር መገለጫ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው ለአገው ሕዝብ ፈረስ ሁለ ነገሩ ነውም ብለዋል። የአገው ሕዝብ ፈረሱን ለሠርግ ሙሽሮችን፤ ለንግሥ ታቦታትን ያጅብበታል፤ በሰላሙ ጊዜ ለጭነት ይገለገልበታል፤ በጦርነት ጊዜ ስንቁን ያጉዝበታል፣ ሲያመውም ወደ ሕክምና የሚያደርሰው ነው፣ ፈረስ ሁሉ ነገሩ ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።

በፈረሰኞች በዓል በአንድ በኩል በየአውደ ውጊያው ለኢትዮጵያ ነፃነት የተሰው ጀግኖች የሚዘከሩበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከጀግኖች አርበኞች ጋር የተዋደቁትን ፈረሶች ውለታ የሚታወስበት መኾኑን ነው ያነሱት። የአገው ሕዝብ ፈረስ በጦርነት ወቅት አድርሶ አይመለስም በአውደ ውጊያው ከጀግኖች ጋር ሲዋደቅ አብሮ ይውላል ብሎ ያምናል ነው ያሉት።የአገው ሕዝብ ይህን በማመኑ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚዘከር በዓል እያካሄደ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በዓል ከበዓልነቱ ባሻገር አባላት እርስ በእርስ ይተዋወቁበታል፣ የተጣላን ያስታርቁበታል፤ ሁነኛ የባሕላዊ የግጭት መፍቻ ቁልፍ አድርገው ይጠቀሙበታል፤ የአሥተዳደር ጥበብንም ለትውልድ ያስተላልፉበታል ነው ያሉት። እንዲህ አይነቱን በዓል ባሕሉ እና ወጉን ጥብቆ እና የሀገር ቅርስ ኾኖ እንዲቀጥል በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን በ2015 ዓ.ም መመዝገቡን አስታውሰዋል።

በዓሉ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን የዓለም አቀፍ ቅርስ መኾን ስለሚገባው የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ፣ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ እየሠሩ መኾኑንም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here