ባሕር ዳር: ጥር 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከጎንደሪያን ዘመን እስከ ላሊበላ፣ ከአክሱም ሥልጣኔ እስከ ሀረር ጀጎል ግንብ እና መሰል በሀገሪቱ የሚታዩ የሥልጣኔ በሮችን ስናይ ይህች ሀገር እውነትም ሊለውጧት የሚጥሩ መሪዎች በየጊዜው ስለመነሳታቸው ማሳያዎች ናቸው። የልማት እና የዕድገት ውጥኖችን ላየ የሚከተል፣ የሚያዘልቅ እና አስፍቶ የሚሠራ ጠፍቶ እንጅ የየዘመናቱ ድንቅ ልጆች የለውጥ እሳቢያቸውን ለማሳየት ጥረት አድርገዋል ለማለት ይቻላል።
ኢትዮጵያውያን መሪዎች ዘመናዊነትን እና የሚጠቅሟቸውን ከውጭ ሀገራት ጭምር የማምጣት እና የማላመድ ችግር አልነበረባቸውም። በዚህ ረገድ ከአጼ ምኒሊክ እስከ አጼ ኃይለሥላሴ ያሉ መሪዎች ከውጭ አምጥተው ያስተዋወቋቸውን ቴክኖሎጅዎች ማየት በቂ ማሳያ ናቸው። ከ2010 ዓ.ም የለውጡ ጊዜ በኋላም ስንዴ አምርቶ በምግብ ራስን ከመቻል እስከ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እስከመገንባት እና ያሉትን እስከመጠገን የተሄደበት ርቀት ለለውጥ እየተሠራ ያለውን ሥራ ማሳያ ናቸው።
እንደ ሲንጋፖር ያሉ ሀገራት ለለውጥ ከሠሩት ሥራ የሚጠቅሙትን ወስዶ ለመተግበር በሚኒስትሮች ደረጃ የተደረገው ጉብኝትም ለውጡን በዕውቀት ታግዞ ለመምራት ያለን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ከ60 ዓመታት በፊት ደሃ የወደብ ከተማ የነበረች ሀገር የፈጣን ዕድገት ተምሳሌት ያደረጋትን መሪ ሊ ክዋን ይው የከተማን ገጽታ በመገንባት እና ለነዋሪዎቿ ምቹ በማድረግ የሠራው ሥራ ለውጥ አምጥቶ የሀገሪቱን ገጽታ መገንባት ችሏል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የከተማ የኮሪደር ልማትም እንደ ሀገር በየከተማዎቹ ለውጥ እንዲቀጣጠል ካለ እሳቤ የመነጨ ሥራ ነው። ሊ ክዋን ዪው ችሎታን መሠረት ያደርገ መንግሥታዊ አሥተዳደር መገንባት ላይም የለውጡ መሠረት ሲኾን ኢትዮጵያም ለመለወጥ ከዚህ የመነጨ ሥራ እየሠራች ስለመኾኑ በተቋማት ላይ የሚታየው የለውጥ ሥራ ጅምር ማሳያ ነው።
በተለይም እንደ ሲንጋፖር አይነት ሀገራት የተገበሩት የቱሪዝም ሥራ ማርሽ ቀያሪ አድርጎ አስቀምጧቸዋል። ኢትዮጵያም አሁን ላይ እየተገበረች ያለችው ይህንኑ የለውጥ እሳቤ ነው። በኢትዮጵያም የተጀመሩትን ከመጨረስ እና የነበሩትን ከማደስ እስከ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እስከ መፍጠር የተሠራው የለውጥ ሥራ በሀገር ውስጥ ለውጥን ለመጫር የተሄደበትን እርቀት ማሳያዎች ናቸው።
እንደ ገበታ ለሀገር እስከ ገበታ ለትውልድ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ለለውጥ እና ዕድገት በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። በአማራ፣ በኦሮምያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገኙት ከጎርጎራ፣ ከሀላላ ኬላ፣ ከጨበራ ጩርጩራ እና ወንጭ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችን ተከትሎ በመላው ኢትዮጵያ ሰባት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ሥራ የዚሁ ለውጥ ማሳያ ተደርገው ይወሰዳሉ።
በተለይም እንደ አማራ ክልል የተሠራው የገበታ ለሀገር ውጤት የኾነው ጎርጎራ አሁን ላይ በአካባቢውም ኾነ በክልሉ የፈጠረው የለውጥ ፍላጎት ነፋስ ነገ ምን አይነት ሀገር እንደሚኖር የሚያሳይ ነው። የጎርጎራ ሥራ ልማትን ጀምሮ ከመጨረስ እስከ ቀጣይ የተሻሉ ልማቶች ማሰብ እና መሥራት እንዲቻል የቤት ሥራ የሰጠ ነው ይላሉ የጎርጎራ ፕሮጀክት የፈጠረውን መነሳሳት የነገሩን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የባሕል ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አቤል መብት።
ኀላፊው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገነባው ጎርጎራ አሁን ላይ ከፈጠረው የሥራ ዕድል ባለፈ በአካባቢው ጣናን ተንተርሶ ሌሎች ሥራዎች አስቦ ለመሥራት ለቀጣናው የቤት ሥራ የሰጠ ነው ይላሉ። ጎርጎራ ከታሰበ እና ከለማ በኋላ በአካባቢው ከፍተኛ የለውጥ ነፋስ እንዲኖር አድር ጓል የሚሉት አቶ አቤል እንደ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሕዝብ ጸጋውን ለመጠቀም እንዲችል የተለያዩ የሥራ ዕድሎች እየተፈጠሩ ነው ይላሉ።
አቶ አቤል ጎርጎራን ተንተርሶ ለቱሪስቶች አገልግሎት የሚሰጡ ወጣት የካሜራ ባለሙያ አጀረጃጀት፣ አስጎብኝ ማኅበራትን እና ከትንንሽ የቢዝነስ ሥራ እስከ ትልልቅ ሀገራዊ ምርቶችን የሚያመርቱ ወጣቶችን በማደራጀት ቀጣናውን የሥራ ዕድል እና የዕድገት መፍጠሪያ ለማድረግ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
ጎርጎራ አካባቢውን ይበልጥ ለማልማት እና ለመጠቀም አይን የገለጠ በመኾኑ ሌሎች ልማቶችንም ለማከናወን ሰፊ ጥረት መጀመራቸውን ነው የነገሩን። በተለይም ቀጣናው ለአሳ ምርት ሁነኛ በመኾኑ የአካባቢው መገለጫ አድርጎ የመጠቀም እሳቤዎችም ስለመኖራቸው ተናግረዋል።
በቀጣይም ጎርጎራን ይበልጥ ጥቅም ላይ ለማዋል በአካባቢው ለቱሪስቶች የሚኾኑ የዕደ ጥበብ ሥራዎች፣ ባሕላዊ ምግብ ቤቶች እና ልዩ ልዩ የሥራ ዕድሎችን ፈጥሮ ለመሥራት ጥረቱ መቀጠሉን አስገንዝበዋል።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!