በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ለመልማት የተመረጠው ሎጎ ሐይቅ!

0
344

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሎጎ ሐይቅ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ የሚገኝ ሐይቅ ነው። ሐይቁ ከደሴ ከተማ ወደ ወልዲያ በሚወስደው ዋና መንገድ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ሐይቅ ከተማ 2 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ሎጎ ሐይቅ በሰንሰለታማ ተራሮች መሐል የሚገኝ ማራኪ እይታ ያለው ሐይቅ ነው። ከባሕር ወለል በላይ 1950 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ውብ ሐይቅ ነው። 35 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋትም አለው። አማካይ ጥልቀቱ ከ23 ሜትር እስከ 88 ሜትር ይደርሳል፡፡

በሎጎ ሐይቅ ውስጥ ሦስት አይነት የዓሳ ዝርያዎች ይገኛሉ። እነሱም ቀረሶ፣ ዱቤና አምባዛ የዓሳ ዝርያዎች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ሐይቁ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የዓሳ ምርት በመስጠት የገቢ ምንጭ ከመኾኑ በተጨማሪ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል ፈጥሯል።

ለጎብኝዎችና ለአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ በሐይቁ ዳርቻ የተገነቡ መለስተኛ ሎጆች፣ ሆቴሎችና ካፍቴሪያዎች አሉት። በዓሳ ማስገር ሥራ የተሰማሩ ወጣቶች፣ የመጓጓዥያና የመዝናኛ አገልግሎት የሚሰጡ የጀልባ ባለቤቶች ይገኛሉ።

ለሐይቁ ልዩ ውበት የሆነው ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም በዚሁ ሐይቅ ይገኛል። ገዳሙ ታሪካዊ ገዳም ሲሆን በአጼ ድልናኦድ ዘመነ መንግሥት የተመሰረተ እና የቀደምት ገናና ታሪክ ባለቤት እንደኾነም ይነገራል።

የሎጎ ሐይቅ ለእይታ ውብና ማራኪ በመኾኑ እንዲሁም በዙሪያው ያሉ ተራራማ መልካምድራዊ ገጽታዎች ለአካባቢው ለቱሪዝም መስህብነት የሚያገለግሉ ተፈጥራዊ ጸጋዎቹ ናቸው።

የሎጎ ሐይቅን በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አማካኝነት ለማልማት ተመርጦ ወደሥራ ተገብቷል። ይህ በመኾኑም ሐይቁ ካለው ተፈጥሯዊ ውበቱና ማራኪ መልካምድራዊ ገጽታዎቹ ተጨማሪ ለአካባቢው ሕዝብ ተደማሪ ውበት፣ ሀብት፣ የቱሪዝም መስህብና ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር ያስችላል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መሥተዳድር ምክርቤትም በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት እንዲለማ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መመረጡን ተከትሎ ፕሮጀክቱ የሚያካልለውን ቦታ ከሦስተኛ ወገን ነጻ ለማድረግ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ውሳኔ አሳልፏል።

የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት ታኅሣሥ 13/2016 ዓ.ም ባካሔደው ጉባኤ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ካሣ ክፍያ የሚሸፍን በጀት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

ሎጎ ሐይቅና አካባቢው የድንቅ ምድርና የውብ ተፈጥሯዊ ጸጋ ባለቤት ነው። በተፈጥሮ በጸጋው ልክ አምሮና ተውቦ አብቦና ደምቆ የምናይበት ጊዜው ሩቅ እንደማይኾን ከአማራ ክልል ፕሬዚደንት ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here