“ጎራዳ”

0
180

ባሕር ዳር: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ክልል ውብ ባሕል ያለው ክልል ነው። በተለይም ከማይዳሰሱ ቅርሶች ጋር በተገናኘ በርካታ ቅርሶችም የሚገኙበት ነው፡፡ አንዲት ሴት ከአማራ ክልል ስለመኾኗ የምትታወቅበት ባሕላዊ አልባስ ነው፡ ጎራዳ። አሁን ላይ ጎራዳን የምናስተውለው በገጠሩ የአማራ ክልል አካባቢ ነው፡፡

ይህ አልባስ በእጅ ጥጥ ተዳምጦ እና በእንዝርት ተፈትሎ እና ተቀልሞ በጥሩ ሸማ ሠሪ የሚሠራ ሲለብሱት ውበት የሚያላብስ ባሕላዊ የአልባሳት ዓይነት ነው፡፡ ይህ አልባስ በገጠሩ አካባቢ በሥራም ኾነ በሌሎች ባሕላዊ ክዋኔዎች መለበስ የሚችል ነው ይላሉ በአማራ ክልል የጎንደር እና አካባቢዎች የቱሪስት አስጎብኝ ሰብለ ግርማ፡፡

የቱሪስት አስጎብኝዋ ሰብለ ግርማ እንደሚሉት ሴቶች ሲፈጩም ኾነ የእርሻ ሥራ ሲያከናውኑ እያሳጠሩ እና እያስረዘሙ የሚለብሱት የአልባስ አይነትም ነው፡፡ ይህ አለባበስ የተለያየ የጥልፍ አይነት ያለው ሲኾን ይህም በእጃቸው የሚጠለፍ ነው፡፡ ጎራዳ ተብሎ የሚጠራው ልብስ በጋብቻም ኾነ በእድሜ ሁኔታ የተለያየ ነው፡፡ በተለይም በመካከለኛ እና በትዳር ውስጥ ያለች ሴት የምትለብሰው የጎራዳ አጠላለፍ ቀጠን ያለ አጠላለፍ ዓይነት ያለው ሲኾን ሰኔል ሥራ ተብሎም ይጠራል፡፡

ያላገቡ እና ጉብል ተብለው የሚጠሩ ሴቶች ደግሞ ከትክሻ እና ከትክሻ አካባቢ የሚወርድ ደመቅ ያለ ጥልፍ ያለው ሲኾን ወደታች ያለው ጥልፍ ደግሞ ሰፋ ያለ አጠላለፍ ያለው ነው፡፡ ጎራዳ የሚባለው ልብስ እጅየው ላይም በተለያየ የሀገር ውስጥ ክር በሚያምር የጥልፍ ዓይነት አምሮ ይጠለፋል፡፡

በተለይም ጎራዳ አጃቢ አለባበስ ያለው ሲኾን ከጭንቅላት ላይ ሸብ የሚደረግ ሻሽ የተባለ ጥምጣም ያለው ሲኾን አንገት ላይ የሚደረጉ መስቀሎችም ይኖሩታል፡፡ መስቀሎቹ በማግባት እና በዕድሜ የሚወሰኑ ናቸው፡፡ ያገቡ ሴቶች አንድ መስቀል የምታደርግ ሲኾን አንዳንድ ጊዜም ማርትሬዛ ሊጨምሩበት ይችላሉ፡፡

ያላገባች ከኾነ ግን በመጠናቸው የተለያዩ ሦስት መስቀሎችን በአንገቷ ታደርጋለች፡፡ በተለይም ሽርብ ድሪ ድንብል የሚባል ቀለበት መስል የሚጨመርበት ኾኖ ተሠርቶ ይታሠራል። ይህም ያገባች ሴት የምታስረው ነው፡፡ ሌላው አሸንክታብ የሚባል ሲኾን ይህም ከአንገት የሚታሰር ኾኖ በቆዳ የሚሠራ ነው፡፡

ድባ፣ ዛጎል፣ እርባ፣ መዳብ እና ዛጎል ተደርጎ በአንድ ላይ ከተሠራ በኃላ ከአሸንክታቡ ጋር ተደርጎ ተሠርቶ በአንገት የሚደረግ ሲኾን ያገቡም ኾነ ያላገቡ ሰዎች ሊለብሱት የሚችሉት ነው፡፡ ሌላው የጎራዳ ማድመቂያ ድኮት የሚባል ሲኾን 11 ድርድር ያለው ኾኖ ይሠራል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here