ባሕር ዳር: የካቲት 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ብዙ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ጸጋ ያላት ሀገር ናት፡፡ ከተፈጥሮ ጸጋዎቿ መካከል ብዛት ያላቸው ሰንሰለታማ ተራሮች፣ አምባዎች፣ ሸለቆዎች፣ ወንዞች፣ ሐይቆች፣ ፏፏቴዎች፣ ፣ እንስሳት ፣ አዕዋፋት እና ዕፅዋት ይጠቀሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋ ካደላቸው እና በግንባር ቀደምትነት ከሚጎበኙ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች መካከል ደግሞ የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አንዱ ነው።
ፓርኩ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ይገኛል። ከአዲስ አበባ በ870 ኪሎ ሜትር፣ ከጎንደር 122 ኪሎ ሜትር፣ ከዞኑ ከተማ ደባርቅ ደግሞ በ22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ፓርኩ አስገራሚ ገደላማ፣ ሸለቆ፣ አምባ፣ ተራራ፣ ወጣ ገባ የመሬት ገጽታዎችን እና አስደናቂ የብዝኃ ሕይወት ስብጥርን ይዟል፡፡ በተለይም ደግሞ ለዐይን የሚማርኩ፣ ውብ እና አስገራሚ ለስብሰባ የተቀመጡ የሚመስሉ ሰንሰለታማ ተራራዎች፣ አስፈሪ ገደላ ገደሎች የሚበዙበት ሲኾን የተወሰነው የፓርኩ አካባቢ ደግሞ ቆላማ ሥፍራዎችን ይዟል።
የፓርኩ አማካይ የዝናብ መጠን 1 ሺህ 550 ሚሊ ሜትር ነው። 75 በመቶ የሚኾነው የዝናብ መጠን የሚዘንበው ደግሞ ከሰኔ እስከ መስከረም ባለው የክረምት ወቅት ነው፡፡ የአየር ንብረቱ በአብዛኛው ተመሳሳይ ቢሆንም የቀኑ እና የማታው የአየር ንብረት ግን ይለያያል፡፡ ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ ያለው ወቅት በጣም ቀዝቃዛ ነው፡፡ የፓርኩ የሙቀት መጠን ከወቅት ወቅት የተለያየ ነው። ከፍተኛው በአማካይ 15 ዲግሪ ሴንትግሬድ፣ ዝቅተኛው ደግሞ 3 ዲግሪ ሴንትግሬድ ይመዘገባል፡፡
የፓርኩ የመሬት አቀማመጥ ከፍተኛ ነውና “የአፍሪካ ጣሪያ” የሚል ስያሜ እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ በብሔራዊ ፓርኩ ከሚገኙ ተራራዎች መካከል ራስ ደጀን 4 ሺህ 543 ሜትር፣ ወይኖ በር 4 ሺህ 465 ሜትር፣ ቅዱስ ያሬድ 4 ሺህ 453 ሜትር፣ አናሉ 4 ሺህ 449 ሜትር፣ ጠፋሁ ለዘር 4 ሺህ 449 ሜትር፣ ቧሂት 4 ሺህ 430 ሜትር፣ ስልቂ 4 ሺህ 420 ሜትር፣ መሳረሪያ 4 ሺህ 353 ሜትር፣ በሮች ውኃ 4 ሺህ 272 ሜትር፣ ዋልያ ቀንድ 4 ሺህ 249 ሜትር ይገኙበታል። ከራስ ደጀን ጋር የተያያዙ አባት ደጀን እና ግልገል ደጀን የተባሉ ተራራዎችም አሉ።
ፓርኩ በደባርቅ፣ በጃንአሞራ፣ በበየዳ፣ በጠለምት እና አዳርቃይ ወረዳዎች የሚገኙ 38 የሚኾኑ ቀበሌዎችን ያካትታል ፓርኩ በ1959 ዓ.ም በብሔራዊ ፖርክነት የተከለለ ሲሆን በ1962 ዓ.ም በትእዛዝ ቁጥር 59/62 ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ በ1970 ዓ.ም ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዬኒስኮ) በዓለም አቀፍ ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡ የፓርኩን አጠቃላይ ብዝኃ ሕይወት በተመለከተ በቀጣይ ክፍል የምናጋራቹህ ይኾናል።
በመረጃ ምንጭነት የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕል እና የተፈጥሮ መስህብ እና የአማራ ድንቅ ምድር የሚሉትን መጽሐፍት ተጠቅመናል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!