ባሕር ዳር፡ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ብዙ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ፀጋ ያላት ሀገር ናት፡፡ በሀገሪቱ የተፈጥሮ ፀጋ ከተጎናጸፉ የጎብኝዎች መዳረሻ ሥፍራዎች መካከል የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አንዱ ነው። ፓርኩ የተለያዩ ብዝኀ ሕይዎት እና አስደናቂ መልክዓ ምድሮችን የያዘ ድንቅ ሥፍራ ነው።
የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እንደ ጓሳ እና ጠምበለል የተባሉ በፓርኩ ብቻ የሚገኙ ዕፅዋትን ጨምሮ ከ1 ሺህ 200 በላይ የሚኾኑ ልዩ ልዩ ዕፅዋትን ይዟል፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንደ ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጆሮ እና የምኒልክ ድኩላን ጨምሮ 22 የሚኾኑ ታላላቅ አጥቢ እንስሳትም መገኛ ነው። 27 የሚኾኑ የውኃ ምንጮች መፍለቂያ ነው፡፡
ፓርኩ 180 የሚጠጉ አዕዋፋትም በውስጡ ይገኙበታል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ባለረጅም ጥፍር የሐበሻ ወፍ፣ የሐበሻ ግንደ ቆርቁር፣ የሐበሻ ድመት መሳይ ወፍ፣ ራሰ ጥቁር ጨረባ፣ የአንኮበር ሰሪን እና ደረተ ጠቃጠቆ ኩልሊት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ብቻ ከሚገኙት ብርቅዬ የአዕዋፋት ዝርያዎች በተጨማሪ እንደ ኩልኩልቴ ጋጋኖ፣ ባለነጭ ኳሌታ እርግብ፣ ራስ ጥቁር ሸሻይ፣ ክንፈ ነጭ የቋጥኝ ወፍ፣ ዝንጉርጉር ድንቢጥ፣ ግንባረ ጥቁር ጭሬ፣ መንቁረ ደንዳና ቁራ፣ መንቁረ ነጭ ዋርዳ፣ ቡንኝ ጥራጥሬ በሊታ ዎፍ፣ የሐበሻ ጥቁር ራስ ዘርበል፣ ክንፈ ጥቁር በቀቀን፣ ጀርባ ነጭ ድንቢጥ የመሳሰሉ አእዋፋት መገኛ ነው።
የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በርካታ ወንዞች፣ ፏፏቴዎች፣ ጅረቶች እና ምንጮች የሚገኙበትም ቦታ ነው፡፡ ከተራሮች የሚፈልቁት ምንጮች የተከዜ ወንዝ መነሻ ናቸው፡፡ በስሜን ተራሮች ፓርክ ውስጥ ዓመቱን ሙሉ ሳይደርቁ ከሚፈስሱ ወንዞች ውስጥ ደግሞ የአንስያ፣ የመሽሃ እና የላሞ ወንዞች ዋና ዋናዎቹ ይገኙበታል፡፡
ፓርኩ አስደናቂ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ አለው፡፡ ጭልቋኒት፣ አይመትሬ፣ ጂንባር ፏፏቴ፣ ቀዳዲት፣ ሰሃ፣ ኢሜት ጎጎ፣ እናትዬ፣ ሶና እና ሃዋዛ የበለጠ ማራኪ እይታ ያላቸው እና በብዛት ጎብኝዎች ጊዜ ወስደው የሚመለከቷቸው ቦታዎች በቅደም ተከተል ይጠቀሳሉ። በፓርኩ መታየት ከሚገባቸው ማራኪ ቦታዎች ውስጥ ጂንባር ፏፏቴ ሌላኛው አንዱ ነው፡፡ 530 ሜትር ከፍታ አለው። በከፍታውም ከቪክቶሪያ ፏፏቴ በ110 ሜትር ይበልጣል። በክረምት ወራት ደግሞ ፏፏቴው ጎልቶ ይታያል።
ኢሜት ጉጎ ማራኪ እይታ ካላቸው ቦታዎች የሚልቅ ሲኾን ከባሕር ጠለል በ3 ሺህ 926 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡ ኢሜት ጉጎ ላይ ኾኖ ለተመለከተ ሰው ራስ ደጀንን ጨምሮ 360 ዲግሪ ሁሉንም ቦታዎች ማየት ያስችላል፡፡ በመረጃ ምንጭነት የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕል እና የተፈጥሮ መስህብ እና የአማራ ድንቅ ምድር የሚሉትን መጽሐፍት ተጠቅመናል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!