ጢስ ዓባይ ፏፏቴ

0
137

ባሕር ዳር: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓባይ ወንዝ በክረምት በአማካይ 400 ሜትር በሚሸፍን ስፋት ወደ ጢስ ዓባይ ፏፏቴ ይጓዛል። ከ40 እስከ 50 ሜትር ጥልቀት ወዳለው ገደል ሲወረወር የሚፈጥረው ፍንጣቂ አካባቢውን በጢስ ይሸፍናል። በተለይም ደግሞ በክረምት ወራት የሚወርደው የውኃ ጅረት ነጎድጓዳማ ድምጽ እና ቀስተ ደመና ከአካባቢው ልምላሜ ጋር ተደምሮ የማይጠገብ የመንፈስ ርካታ ይሰጣል፡፡

የጢስ ዓባይ ፏፏቴ ዓመቱን በሙሉ መጎብኘት የሚችል ቢኾንም ከዓባይ ወንዝ መሙላት እና መጉደል ጋር ተያይዞ ውበቱ አብሮ ይቀያየራል። ወንዙ ከሰኔ እስከ ነሐሴ ሞልቶ መደፍረስ ሲጀምር ፏፏቴው ወርቃማ መልክ ይይዛል። ከመስከረም እስከ ኅዳር ደግሞ አካባቢው በልምላሜ እና አበባ ተውቦ ፏፏቴው ነጭ አረፋ እየዳፈቀ የሚታይበት ወቅት ነው።

ፏፏቴው ከባሕር ዳር ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ 30 ኪሎ ሜትር ከምትገኘው የጢስ ዓባይ ከተማ አቅራቢያ ነው የሚገኘው። ወደ ሥፍራው ለመጓዝ ከጢስ ዓባይ ከተማ ሁለት አማራጮችን መጠቀም ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው አማራጭ ከከተማው ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በእግር በመጓዝ የዓባይን ወንዝ በጀልባ በመሻገር ወደ ፏፏቴው የሚያደርስ ነው። በዚህ አማራጭ የአካባቢውን ልምላሜ እና በርጋታ የሚፈሰውን የዓባይ ወንዝ የመጎብኘት እድል ይሰጣል፡፡

ሁለተኛው አማራጭ ከከተማዋ የ1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ከተሽከርካሪ ጉዞ በኋላ ጥንታዊውን የዓለታ ድልድይ በመሻገር በእግር ወደ ፏፏቴው ያደርሳል፡፡ በዚህ አማራጭ የጢስ ዓባይ የአለታን ድልድይ፣ ዓባይን በዓለቶች መካከል ሲጓዝ የሚያሳየውን ትርኢት፣ የጢስ ዓባይ ከተማን፣ የመጀመሪያውን የኃይል ማመንጫ እንዲሁም የፏፏቴው ሙሉ ገጽታን በፎቶ እያስቀሩ ለመጎብኘት እድል እንደሚሰጥ የአማራ ድንቅ ምድር መጽሐፍ መረጃ ያሳያል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here