ባሕር ዳር: የካቲት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለዓድዋ ጦርነት መነሻ የኾነው የውጫሌ ውል የተጻፈበት ታሪካዊ ቦታ ነው ይስማ ንጉሥ። ይስማ ንጉሥ በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ከደሴ-ወልዲያ መንገድ 6ዐ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ውጫሌ ከተማ ለመድረስ 7 ኪሎ ሜትር ሲቀር ከዋናው መንገድ 4 ኪሎ ሜትር ወደ ግራ ገባ ብሎ ከአምባሰል ተራራ ግርጌ የሚገኝ ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡
ለታሪካዊው የዓድዋ ጦርነት መነሻ በመኾን ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የውጫሌ ውል ቀዳሚው ነው፡፡ የውጫሌ ውል በንጉሥ ምኒልክ እና በጣሊያን ንጉሥ ኡምቤርቶ ወኪል ኮንት አንቶሎኒ መካከል ውጫሌ በሚባል ቦታ ሚያዚያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም የተደረገ የውል ስምምነት ነው፡፡
በውሉ ከተፈረመው ከ20ዎቹ የውጫሌ ውል አንቀጾች መካከል በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳው አንቀጽ 17 ነው፡፡ በአንቀጽ 17 አማካኝነት ጣሊያን የትርጉም ልዩነት ያለው ቃል በመጠቀም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመጣስ የጣልያን ሞግዚት እንድትኾን እያመቻቸች መኾኑ በኢትዮጵያ በኩል ታወቀ፡፡
የጣሊያንን መሰሪ አካሄድ ዘግይተው የተረዱት ነገሥታቱ እና መኳንንቱም የውጫሌ ውልን እንደማይቀበሉት ለጣልያን መንግሥትም፣ ለመላው ዓለምም አሳወቁ፡፡ ጉዳዩም ለነፃነቱ ቀናኢ በኾነው በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ፡፡ የውጫሌ ውል እንዲፈርስ እና ኢትዮጵያ ለማይቀረው ጦርነት እንድትዘጋጅ ተወሰነ፡፡
በወቅቱ ውሉ እንዲፈርስ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ታሪክ ይናገራል፡፡ እቴጌ ጣይቱ “እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም፤ ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከምቀበል ጦርነት እመርጣለሁ፡፡ ይስሙ ንጉሥ!” የሚል ታሪካዊ ንግግር አድርገዋል፡፡ ይሄን ንግግራቸውን ተከትሎም የውጫሌ ውል የተጻፈበት ቦታ “ይስማ ንጉሥ” በሚል እንደተሰየመ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ዳግማዊ ምኒልክም የባለቤታቸውን እና መኳንንቱን ሐሳብ ተቀብለው ውሉን በመሰረዝ የዓድዋ ጦርነትን ታሪካዊ የክተት አዋጅ አስነግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮም ይህ ቦታ ታሪኩ ተጠብቆ እና ለምቶ የቱሪስት መዳረሻ እንዲኾን በማሰብ በይስማ ንጉሥ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በማስመደብ ደረጃውን የጠበቀ ሙዚየም አስገንብቷል፡፡ የዚህ ታሪክ ባለቤት የኾኑትን እቴጌ ጣይቱ ብጡል እና አጼ ምኒልክንም የሚዘክር ሐውልት በዚሁ ቦታ ላይ ተሠርቶላቸዋል፡፡
የአምባሰል ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን በድረ ገጹ እንደገለጸው የይስማ ንጉሥ ሙዝየም የአካባቢውን ባሕል ለማስተዋወቅ፣ ሀገራዊ ፍቅር እና አንድነትን ለማስተማር፣ ታሪክን ለማስረዳት እና ለቀጣይ ትውልድ ጠብቆ ለማቆየት የጎላ ሚና እንዲኖረው ታስቦ ተገንብቷል፡፡ ከውጫሌ ውል እስከ ዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ታሪክን ሊገልጽ በሚችል መልኩ የተደራጀው ማዕከሉ በተለይም የጥቁሮችን የአሸናፊነት መንፈስ የሚያንጸባርቁ ይዘቶች አሉት፡፡
የመረጃ ምንጮቻችን የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እና የአምባሰል ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ድረ ገጾች ናቸው።
በደመወዝ የቆየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን